የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ውድድር ባለፈ በረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ሊሠሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ውድድር ባለፈ በረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ሊሠሩ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ውድድር ባለፈ በረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመለከቱ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ለዕድገት መምራት” በሚል መሪ ቃል ዛሬ መካሔድ በጀመረው 2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ላይ በመገኘት ንግግር ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ይህንን ታላቅ አህጉራዊ መድረክ ማስተናገዷ ለሁላችንም ታላቅ ኩራት ነው ብለዋል።
በመደመር እሳቤ እየተመራን፤ ሕዝባዊ አንድነትን፣ ተጠያቂነትንና አካታች አስተዳደርን ማረጋገጥ የፖለቲካ አመራር የዜጎችን ሕይወት እንዲያሻሽል የሚያስችሉ ወሳኝ መሠረቶች ናቸው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ይህም ፓርቲዎች ከምርጫ ውድድር ባለፈ አሻግረው እንዲመለከቱ፣ በመንግሥት ለውጦች የማይቀያየሩ፣ ብሔራዊና ቅድሚያ በሚሰጣቸው የረጅም ጊዜ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት እንዲፈጥሩ እና ለሀገር ጥቅም በጋራ እንዲሠሩ የሚጠይቅ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት።
በሌላ በኩል፣ ተተኪው ትውልድ ኃላፊነቶችን እየወሰደ የሚያድግበትን ዕድሎችን እያገኘ እንዲሄድ ለማድረግ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እጅግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አመራር የልህቀት አካዳሚ በኩል የምትሰጠውን ሥልጠና በአህጉሪቱ ለሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክፍት ማድረጓን እንደምትቀጥል አስታውቀዋል።
ለሕዝባችን የተሻለ መጻኢ ዕድል የመገንባት ኃላፊነታችን ሊቀጥል ይገባል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።