ቀጥታ፡

የልማት እንቅስቃሴዎችን ከመንግሥት ጎን በመሆን መደገፍ የሁሉም ኃላፊነት ነው - ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦​በሀገሪቱ የተጀመሩ የልማትና ዘላቂ ሰላም ግንባታ ስራዎችን ከመንግሥት ጎን በመሆን መደገፍ የሁሉም ሀላፊነት መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ አስገነዘቡ።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት 2ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል።


 

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ለእስልምና እሴቶች፣ ለሀገር አንድነት እና ለሰላም ቅድሚያ የሚሰጥ ነው።

​በሀገሪቱ የተጀመሩትን የልማትና የዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደትን ከመንግሥት ጎን በመቆም መደገፍ የሁሉም ሀላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ምክር ቤቱ አካሂዶት የነበረው ግልጽና አሳታፊ ምርጫ፣ የሐጅ አፈጻጸም ሂደቱ ያስመዘገበው ከፍተኛ ስኬት፣ እንዲሁም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ያከናወናቸው የሕዝብ ለሕዝብና የዲፕሎማሲ ሥራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን አንስተዋል።


 

በሰላም ሚኒስቴር የሃይማኖት እና እምነት ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈፃሚ አምባሳደር እሸቱ ደሴ፣ ሃይማኖት ለሰላማዊ ማኅበረሰብ ግንባታ እና ለሀገራዊ አንድነት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከጠቅላይ ምክር ቤቱ ጋር በሰላም ግንባታና በሀገራዊ መግባባት ሂደቶች ላይ ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም