ቀጥታ፡

በክልሉ የግብይት ሥርዓቱን ለማሳለጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ

አርባ ምንጭ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እና የግብይት ሥርዓቱን ለማሳለጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ገለጸ።

በቢሮው የገበያ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ድጋፍ ክትትልና አስተዳደር ዳይሬክተር አስናቀ ለገሠ ለኢዜአ እንዳሉት፣ በዞኑ የምርት አቅርቦትና ሰንሰለትን በማሳለጥ ገበያውን ለማረጋጋት ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በተለይ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በክልሉ በማህበራት፣ ዩኒየኖች እና አምራቾች እንዲቀርቡ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም 120 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን በማመቻቸት ሸማቹ ህብረተሰብ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገዛ መደረጉን ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ገበያን ለማረጋጋት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአንደኛው ሩብ ዓመት ብቻ በ25 ሺህ የንግድ ድርጅቶች ላይ ቁጥጥርና ክትትል ተደርጓል ብለዋል።

በዚህም ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ፣ በህገ-ወጥ መንገድ ምርቶችን የሚያዘዋውሩ፣ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ባዕድ ነገሮችን የሚሸጡና ጊዜያቸው ያለፈባቸው ዕቃዎችን ሲሸጡ በተገኙ 1ሺህ 275 የንግድ ድርጅቶች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን አመልክተዋል።

በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ላንተ ቀበሌ ነዋሪ ብዙነሽ ቡንዳሶ እና የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ ሰላምነሽ አትርሳው በበኩላቸው  የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በየከተሞች መቋቋማቸው ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸመት እንዳስቻላቸው ጠቁመዋል።

በተለይ አምራቾች በቀጥታ ምርቶችን ለገበያ ማቅረባቸው ሰው ሰራሽ እጥረትና የዋጋ ጭማሪን በማስቀረቱ  እፎይታ ሰጥቶናል ብለዋል።

ገበያዎቹ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ከመደበኛው ገበያ በተወሰነ ቅናሽ የሚያቀርቡ በመሆናቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከአቅራቢ ማህበራት እና ዩኒየኖች መካከል በአርባ ምንጭ የቤቴል ሸማች ማህበር ሰብሳቢ ተረፈ ቦላኔ እና የጋሞ ሸማቾች ሕብረት ሥራ ዩኒየን ሻጭ ሠራተኛ እምነት አዴ፤ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በስፋት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረቡ  መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም