በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የታየውን የማህበረሰብ ተሳትፎ በበጋ ወራትም ማስቀጠል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የታየውን የማህበረሰብ ተሳትፎ በበጋ ወራትም ማስቀጠል ይገባል
አሶሳ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የታየውን የማህበረሰብ ተሳትፎ በበጋ ወራትም ማስቀጠል እንደሚገባ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳ ተናገሩ።
በክልሉ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማጠቃለያ እና የበጋ ወራት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃግብር በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ እንደገለጹት፤ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የዜጎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር በማቃለል ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በክልሉ በክረምት ወራት በአረጋውያን ቤት ግንባታ እና ዕድሳት፣ በደም ልገሳ እና ሌሎች ዘርፎች የተከናወኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ውጤታማ እንደነበሩ ገልጸዋል።
በክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የታየውን ውጤታማ የህብረተሰብ ተሳትፎ በበጋ ወራትም ለማስቀጠል ይሰራል ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ድንቅነሽ ማሞ በበኩላቸው፤ በክልሉ በክረምት ወራት በተከናወኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች ከ521 ሺህ በላይ የበጎ ፍቃደኞችን ማሰማራት ተችሏል ብለዋል።
በክረምቱ በተከናወኑ የበጎ ፍቃድ ስራዎችም ከ980 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ እና ከመንግስት ሊወጣ የነበረ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ገንዘብ ለማዳን መቻሉን አስታውቀዋል።
በበጋ ወራትም ከ217 ሺህ በላይ በጎ ፍቃደኞችን ለማሰማራት ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በዚህም የማዕድ ማጋራት፣ የሕጻናት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት ፣ የደም ልገሳ፣ የአካባቢ ጽዳት እና ሌሎች ማህበረሰብ ተኮር አገልግሎቶች ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚከናወኑ አስረድተዋል።