ቀጥታ፡

በዞኑ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማልማት ጎን ለጎን የመስተንግዶ ተቋማትን የአገልግሎት ጥራት ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቷል

ሮቤ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማልማትና ከማስተዋወቅ ጎን ለጎን የመስተንግዶ ተቋማትን የአገልግሎት ጥራት ለማሻሻል ትኩረት መሰጠቱን የዞኑ ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።

የመዳወለቡ ዩኒቨርሲቲ በቱሪዝምና መስተንግዶ ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራትና የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል ያለማ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለወጣቶችና ሴቶች እየሰጠ ነው። 

የደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን የቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮብዳ ጃርሶ በወቅቱ እንደገለፁት፤ ቱሪዝም ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገትና ለወጣቶች የሥራ ዕድል መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ዘርፍ ነው።


 

በዞኑ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማልማትና ከማስተዋወቅ ጎን ለጎን የመስተንግዶ ተቋማትን የአገልግሎት ጥራት ማሻሻልና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት የቱሪዝም ልማቱን ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

ለዚህም ቢሮው ከመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በዘርፉ የሚታዩ አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶችን በጥናት በመለየትና ለባለሙያዎች ተግባር ተኮር ስልጠና በመስጠት ዘርፉን ለማዘመን እየሰራ መሆኑን አክለዋል።


 

በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ፣ ጥናት ምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት በዛብህ ወንድሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የቱሪዝም መስክ ከዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከላትና የትኩረት መስኮች አንዱ ነው ብለዋል።

በባሌና በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ በርካታ የተፈጥሮና ታሪካዊ የቱሪዝም መስህቦች እንደሚገኙ አመልክተው እነዚህን ሀብቶች ወደ ገቢ ምንጭና የሥራ ዕድል ለመቀየር ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር የተደገፉ ሥራዎችን ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

ዩኒቨርሲቲው በተለይ በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ በሶፍ ዑመር ዋሻና በድሬ ሼህ ሁሴን መዳረሻዎች አካባቢ የሚታዩ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶችን በጥናት የመለየቱን ተግባር በማሳያነት አንስተዋል።

የቱሪዝም መዳረሻዎች ታሪካዊ እሴታቸው ብቻ ሳይሆን በሚሰጧቸው የመስተንግዶና የሆስፒታሊቲ አገልግሎት ጥራትም ተመራጭ እንደሚሆኑ ጠቁመው፣ በዘርፉ ብቁና በሙያ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ወሳኝ በመሆኑ ስልጠናው መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

ሥልጠናው የአካባቢው ወጣቶችና ሴቶች በቱሪዝምና በሆቴል ኢንዱስትሪው ውስጥ በብቃት ተሰማርተው ፈጣን፣ ተደራሽና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ያለመ መሆኑንም አመልክተዋል።


 

በዩኒቨርሲቲው የቱሪዝምና ብዝኃ ሕይወት ኮሌጅ ዲን ፍቃዱ ለማ በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው የቱሪዝም ዘርፉን በጥናትና ምርምር በመደገፍ ከማሳደግ ባሻገር የዘርፉን የሰው ኃይል የአፈጻጸም ብቃት ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመዳረሻ አካባቢዎች በቱሪዝምና መስተንግዶ ዘርፍ ለተሰማሩ ወጣቶችና ሴቶች እውቀትና ክህሎት በማጎልበት የተቋማትን የአገልግሎት ጥራት ለማሻሻል እንደሚያግዝም ተናግረዋል።

በኢኮ-ቱሪዝም ዘርፍ ተሰማርተው የሥልጠናው ተሳታፊ ከሆኑት ወጣቶች መካከል ሁሴን አህመድ፣ ዩኒቨርሲቲው የሚሰጠው በተግባር የተደገፈ ሥልጠና በተለምዶ በቱሪዝም መዳረሻዎች ሲሠሩ የቆዩትን የሥራ እንቅስቃሴ በዘመናዊ የሙያ ዕውቀትና ክህሎት እንዲያሻሽሉ እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።


 

ሌላዋ የሥልጠናው ተሳታፊ ወጣት ሰሚራ ሐሰን በበኩሏ፣ ሥልጠናው በቱሪዝምና ኢኮ-ቱሪዝም ዘርፍ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት በተለምዶ ከመፈጸም ወደ ዕውቀትና ሙያዊ ክህሎት የተደገፈ አሠራር ለማሸጋገር ጠቃሚ እንደሆነ ጠቁማለች።

ለሦስት ተከታታይ ቀናት የተሰጠው ተግባር ተኮር ሥልጠና የተቀናጀ ቱሪዝም ምንነት፣ ጥራት ያለው መስተንግዶ፣ ቱሪዝምን ወደ ዘላቂ ጥቅም መቀየርና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም