ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሚያስደንቅ የእድገት ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ማየት ችያለሁ 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአስደናቂ የእድገት እና የለውጥ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የሞሮኮው ተመራማሪ እና የዩዝ ፓዮነርስ ኦፍ ሞሮኮ ድርጅት ፕሬዝዳንት ሊማም ቡሲፍ ገለጹ።

ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የሞሮኮው ተመራማሪ እና የዩዝ ፓዮነርስ ኦፍ ሞሮኮ ድርጅት ፕሬዝዳንት ሊማም ቡሲፍ ወደ አዲስ አበባ በመምጣታቸውና ሀገሪቱ እያስመዘገበች ያለውን ከፍተኛ እድገት በአይናቸው በመመልከታቸው መደነቃቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በታዳሽ ኃይል ልማት፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በቴክኖሎጂ እና አካባቢን ከብክለት በመከላከል ረገድ በሞሮኮ እና በኢትዮጵያ መካከል በርካታ የጋራ የትብብር መስኮች እንዳሉ ጠቁመዋል።

ሀገራቱ ይህን የልማት ጎዳና በቀጣዮቹ ዓመታት አጠናክረው ከቀጠሉ የላቀ ሁለንተናዊ ሽግግር ማረጋገጥ እንደሚቻልም ተናግረዋል።

የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በእርስ ልምድ እንዲለዋወጡ፣ ያላቸውን አቅም እንዲያሳድጉ እና የተሻለ የወደፊት እጣ ፈንታ እንዲኖራቸው መድረኩ ትልቅ እድል እንደሚፈጥርም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆኗ እና ለአህጉሩ የሰብአዊ መብት መሻሻል እንዲሁም ለጋራ ትብብር የምታደርገው አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ፣ እንዲህ አይነት አህጉራዊ ጉባኤዎችን በአዲስ አበባ ማዘጋጀቷ ያላትን ሚና በግልጽ እንደሚያሳይ ነው የገለጹት።

በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ጥረቶች እጅግ የሚያስደንቁ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ተሳታፊው አክለውም፣ ከኢትዮጵያ ቆይታቸው ታላቅ ተስፋንና መልካም ስሜትን ይዘው እንደሚመለሱ በመግለጽ፤ በሞሮኮ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም