በአፋር ክልል ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ጥቅም የሚያሳድጉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ጥቅም የሚያሳድጉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ሰመራ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦በአፋር ክልል ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃንፈሬ አሊሚራህ ገለጹ።
የአፋር ክልል የሰው ዘር መገኛ በሆነችው ድንቅነሽ (ሉሲ)፣ በኤርታ አሌ እሳተ-ገሞራ፣ በዳልኦል አስደናቂ ፍልውሃዎች እና በአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ጨምሮ የበርካታ ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻዎች ባለቤት መሆኑ ይታወቃል።
የአፋር ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃንፈሬ አሊሚራህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የክልሉን የቱሪስት መስህቦች በማልማትና በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ የማሳደግና ለስራ ዕድል ፈጠራ ለማዋል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ የተሰራውንና የገበታ ለትውልድ አካል የሆነውን የ“ንኤሌ ፖልም” ሎጅና ሪዞርት ግንባታን ለአብነት ጠቅሰው፣ ይህም የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለማስፋት ከተከናወኑ ስኬታማ ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑን አንስተዋል።
የቱሪዝም ዘርፉ ለዜጎች የሚከፍተውን ሰፊ የስራ ዕድል ጠቀሜታ ለማሳካትም በክልሉ የሚገኙ የሆቴል፣ የባህላዊ ማረፊያዎች እና የምግብ አገልግሎቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ከግል ባለሀብቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ኃላፊው አብራርተዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ነባርና አዳዲስ መስህቦችን በማደስና በመገንባት ወደ ስራ የማስገባት ተግባር መከናወኑን ጠቁመው በአይሳኢታ ከተማ በመደመር መፅሐፍ ሽያጭ ገቢ የታደሰው የሱልጣን አሊሚራህ ሐንፈሬ ቤተ- መንግስት አንደኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በአሎለበድ ፍል ውሃ ሪዞርት ለመገንባት ያሉ ጅምር ስራዎች፣ የኤርታአሌ መዳረሻ ማረፊያ ሎጅ ግንባታ፣ በአደአር ወረዳ የሉሲ መገኛ አካባቢን ለትራንስፖርት ምቹ የማድረግና በሠመራ ከተማ እየተገነባ ያለውን የሉሲ ሙዚየም በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ቢሮው የክልሉን ልዩ የጂኦ-ቱሪዝም ገጽታዎች በዘመናዊ የዲጂታል ሚዲያ አማራጮችና በዓለም አቀፍ መድረኮች የማስተዋወቅ ስራ መጀመሩንም አስታውቀዋል።