በደቡብ ወሎ ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ በቂ ምርት ለገበያ ለማቅረብ ታቅዷል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ወሎ ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ በቂ ምርት ለገበያ ለማቅረብ ታቅዷል
ደሴ ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦በደቡብ ወሎ ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ በቂ ምርት ለገበያ ለማቅረብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአርሶ አደሩ ዘንድ ባህል እየሆነ መጥቷል።
በዞኑ ለስንዴ ልማት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ በቂ ምርት ለገበያ ለማቅረብ ግብ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።
የተሻለ ቴክኖሎጂና ግብዓትን በመጠቀም፣ ለአርሶ አደሩ አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ በማድረግና ግብዓት በወቅቱ በማቅረብ ስንዴን በብዛትና በጥራት ማምረት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም አስረድተዋል።
በዘንድሮው የበጋ ወቅትም 34 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰብ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም አርሶ አደሩ በመኸር ለምቶ የደረሰውን ሰብል ፈጥኖ በመሰብሰብ ወደ መስኖ ልማት እንዲገባ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
የተንታ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ አለባቸው በበኩላቸው፣ በዘንድሮው የበጋ ወራት 1 ሺህ 450 ሄክታር መሬት ስንዴ በማልማት ከ60 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።
ለዚህም በቂ ግብዓት ቀርቦና ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ የእርሻ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።
"በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመን የተሻለ ምርት ለማምረት ተዘጋጅተናል" ያሉት ደግሞ የተንታ ወረዳ የ08 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰይድ መሀመድ ናቸው።
ባለፉት ዓመታት ያገኙትን ልምድ በማስፋት ዘንድሮም አንድ ሄክታር መሬት በስንዴ በማልማት ከ40 ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ማቀዳቸውን ገልጸዋል።
የተሁለደሬ ወረዳ የ09 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አደም አህመድ በበኩላቸው፣ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ዘመናዊ የግብርና አሰራር፣ ማዳበሪያና ሌሎች የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
ከግማሽ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ለማልማት እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጸው፣ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ምርት ለገበያ ለማቅረብ እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።
በዞኑ ባለፈው ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ ከለማው 26 ሺህ ሄክታር መሬት ከ900 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።