በምስራቅ ኦሮሚያ ዞን የማዕድን ሀብቶችን በመለየት የማልማት ስራ በስፋት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ኦሮሚያ ዞን የማዕድን ሀብቶችን በመለየት የማልማት ስራ በስፋት እየተከናወነ ነው
ጭሮ ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ ኦሮሚያ ዞን የሚገኙ የማዕድን ሀብቶችን በማልማት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን የማሳደግ ተግባር በስፋት እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ።
በዞኑ የሚገኙ የተለያዩ የማዕድን ሀብቶችን ለይቶ ወደ ምርት እንዲገቡ፣ እንዲሁም ባለሀብቶች በዘርፉ በስፋት እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል።
በዞኑ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት የማዕድን ፈቃድ አሰጣጥ ባለሙያ ወይዘሮ ምስራ ኡሶ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ የማዕድን ሀብት በስፋት በሚገኝባቸው ሰባት ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ ለማልማት ጥረት እየተደረገ ነው።
የማዕድን ሀብቱ በብዛት በሚገኝባቸው የጭሮ፣ ጡሎ፣ ዶባ፣ ገመቺስ፣ ዳሮ ለቡ፣ ሐዊ ጉዲና፣ ሚኤሶ እና ጉምቢ ቦርዶዴ ወረዳዎች ውስጥ ከ407 ስኩዌር ኪሎ ሜትር በላይ የማዕድን ስፍራዎች ተለይተዋል ብለዋል።
በእነዚህም ወረዳዎች 12 ባለሀብቶች የማዕድን ፈቃድ ወስደው ምርት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በወረዳዎቹ እንደ ድንጋይ ከሰል፣ ጥቁርና ነጭ ድንጋይ፣ ታንታለም፣ ባዛልት፣ ሮያሌት የመሳሰሉ ማዕድናት በስፋት እንደሚገኙ ገልጸው፣ ባለሀብቶች በመስኩ በስፋት እንዲሰማሩ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በተለይም እንደ ጥቁር ድንጋይ፣ ግራናይትና ሌሎች የማዕድን ሀብቶች በብዛት እንደሚገኙ የተጠቆመ ሲሆን፣ እነዚህን ሀብቶች በአግባቡ በማልማት ለኢኮኖሚው የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዞኑ የሚመረቱ የማዕድን ምርቶችም ለድሬዳዋ፣ ለአዳማና ለአዲስ አበባ ገበያ እየቀረቡ ሲሆን፣ ይህም ለገበያ አቅርቦትና ለንግድ እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
የማዕድን ሀብቶች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው ይህም የባለሀብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና የማዕድን ምርትን ለማጓጓዝ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
በወረዳዎቹ በዚህ ዓመት ከማዕድን ልማቱ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት መታቀዱንና በዚህም ባለፉት አራት ወራት ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደተገኘም አብራርተዋል።
በተያዘው ዓመት ለማግኘት የታቀደው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንደሚኖረውም አስረድተዋል።