ቀጥታ፡

አገልግሎትን እያቀላጠፈ የሚገኘው የዲጂታላይዜሽን ስርዓት 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ዲጂታላይዝድ መደረጉ አገልግሎቱን ፈጣንና ቀላል በሆነ መንገድ እንድናገኝ አስችሎናል ሲሉ ተገልጋዮች ገለጹ።

የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዲጂታል ስርዓቱ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ኤፍሬም ጋሪ፤ ኤጀንሲው በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር መዘርጋቱ የልደት እና የጋብቻ ሰርተፊኬትን ህጋዊነት በቀልጣፋ አሰራር ማረጋገጥ ችያለሁ ብለዋል።


 

መንግሥታዊ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ ተደግፈው እንዲሰጡ መደረጉ ከሲቪል ምዝገባና ከነዋሪነት አገልግሎት ጋር በተገናኘ ሲስተዋሉ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፉንም አክለዋል።

ወጣት ሱራፌል ሲሳይ በበኩሉ፤ የልደት ካርድ ለማረጋገጥ ወደ ሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ መምጣቱን ተናግሯል።


 

አሁን ላይ ከሲቪል ምዝገባ ጋር የተገናኙ አገልግሎቶች በዘመናዊ መንገድ የሚሰጡበት ምህዳር በመፈጠሩ ምክንያት ለሚፈልገው መረጃ መክፈል የሚገባውን ክፍያ በቴሌብር በመክፈል ጊዜው ሳይባክን ጉዳዩን በመፈጸሙ መደሰቱን ገልጿል።

አገልግሎቶች እንዲዘምኑ መደረጉ ለህብረተሰቡ እፎይታን የሚሰጥ ነው ያሉት ደግሞ አቶ ዮሴፍ ባዬ ናቸው።


 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጥጋቡ ሹመይ በበኩላቸው፤ መንግሥት ህዝቡ በተቋማት ዘመናዊ አገልግሎት እንዲያገኝ በማስቻል ብልሹ አሰራርን ለመፍታት የወሰዳቸው ተቋማዊ ማሻሻያዎች በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዲቀረፉ አቅም ፈጥረዋል ብለዋል።


 

ኤጀንሲውም ለማህበረሰቡ ቀልጣፋ እና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት በወሰደው ተቋማዊ ሪፎርም የሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎቶችን ከወረቀት አሰራር በማላቀቅ በቴክኖሎጂ ተገልጋይን የሚያስተናግዱበት ሁኔታ ተመቻችቷል ብለዋል።

በተጨማሪም ተገልጋዮች ባሉበት ቦታ ሆነው የመታወቂያ እድሳት፣ የልደት እና ያላገባ ማስረጃን በኦንላይን ሲስተም ማግኘት እንደሚችሉ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ የተሟላና ወቅቱን የጠበቀ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሥርዓት እንዲኖር ኤጀንሲው ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

በሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የመረጃ እና ማስረጃ ማረጋገጫ  ባለሙያ የሆኑት  ስንቄ ደምሰው ፤ በቴክኖሎጂ በተደገፈ መልኩ ከኩነት ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ የሚጠይቃቸውን መረጃዎች በማጣራት ተገልጋይን እያገለገልን እንገኛለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም