ቀጥታ፡

በድሬዳዋ አስተዳደር በበጀት አመቱ ሦስት ወራት ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

ድሬዳዋ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ አስተዳደር በበጀት አመቱ ሦስት ወራት ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የአስተዳደሩ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሉካ መሐመድ አስታወቁ።

የከተማዋ ግብር ከፋዮች በበኩላቸው አመታዊ ግብርን በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈል ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአስተዳደሩ የገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሉካ መሐመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤  ባለስልጣኑ በበጀት አመቱ ሦስት ወራት  ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰብስቧል።

ገቢው ቀጥታና ቀጥታ ካልሆኑ ታክሶች እንዲሁም ታክስ ካልሆኑ ገቢዎችና ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች የተሰበሰበ መሆኑን ተናግረዋል።  


 

የተሰበሰበው ገቢ የዕቅዱ 86 በመቶ መሆኑን ጠቁመው በቀሪዎቹ ወራት በተሻለ ለመሰብሰብ ከወዲሁ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ ለግብር ከፋዮች በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር በመፍጠር ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የአስተዳደሩ ግብር ከፋዮችም አመታዊ ግብርን በታማኝነት በወቅቱ በመክፈል ኃላፊነታቸውን እየተወጡ  መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

የትምህርት ቤት ባለቤት የሆኑት መምህርት በሻዱ ዳዲ፤ የግብር አሰባሰብ ሂደቱ ፈጣንና ግልጽ መሆኑን ጠቁመው እርሳቸውም ግብራቸውን በወቅቱ በመክፈል ሀላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ወንድዬ ተስፋዬ  በበኩላቸው፤ ከግብር የሚሰበሰብ ገቢ ለልማት መፋጠን ወሳኝ በመሆኑ ግብራቸውን በወቅቱ በታማኝነት እየከፈሉ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የንግዱ ማህበረሰብ ያለበትን ኃላፊነት በታማኝነት በመወጣት እየታየ ያለውን ልማት ማገዝ አለበት ያሉት ደግሞ ሌላው ግብር ከፋይ አቶ ገሰሰ ላቀው ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም