በዓድዋ መንፈስ ለአፍሪካ ዘላቂ ብልፅግና፡የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ትልሞች - ኢዜአ አማርኛ
በዓድዋ መንፈስ ለአፍሪካ ዘላቂ ብልፅግና፡የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ትልሞች
አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መዲና ብቻ ሳትሆን፣ የአፍሪካውያን የጋራ መኖሪያ፣ የአህጉሪቱ የውይይት፣የትብብር፣ የዲፕሎማሲና የጋራ መፍትሔ ማመንጫ ማዕከል እየሆነች መጥታለች።
በመደመር መንግሥት የከተማ ልማት ዕመርታ አዲስ አበባ በአጭር ጊዜ ያስመዘገበቻቸው የልማት ስኬቶች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ዓለም አቀፍ የመዳረሻነት አቅሟን ከፍ አድርገዋል።
የተሻሻሉ መሠረተ ልማቶች፣ ዘመናዊ የከተማ ኮሪደሮች፣ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች፣ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች፣ የመንገድና የትራንስፖርት አውታሮች፣ የመዝናኛና የቱሪዝም መስህቦች ከተማዋን ውብ፣ ምቹ፣ ዘመናዊና ለዓለም አቀፍ ኩነቶች ተመራጭ ማዕከል እያደረጓት ነው።
ዛሬ አዲስ አበባ የአፍሪካ መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የቢዝነስ ማኅበረሰቡ፣ የባለሀብቶች፣ የቱሪስቶችና የልማት አጋሮች መገናኛ ስፍራ ከመሆን ባለፈ፣ የአህጉሪቱ የጋራ ተስፋና የጋራ ዕጣ ፈንታ የሚመከርባት መድረክ ናት። ይህም የኮንፈረንስ ቱሪዝምን በማሳደግ፣ የከተማዋን ኢኮኖሚ በማነቃቃት፣ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠርና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን በማጠናከር ረገድ ትልቅ አቅም ነው።
ዓድዋ የአፍሪካ አንድነት፣ነፃነትና የጋራ የወደፊት ራዕይ ምልክት ነው። የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲስ አበባ፣በታሪካዊው የጥቁር ሕዝቦች የድልና የነፃነት ምልክት በሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ጉባኤ ማካሄዳቸው ከተራ የስብሰባ ቦታ ምርጫ በላይ ጥልቅ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና አህጉራዊ ትርጉም አለው።
ዓድዋ አፍሪካውያን በአንድነት፣ በጀግንነትና በራስ የመወሰን አቅም የቅኝ ግዛትን ምኞት ያከሸፉበት፣ ለጥቁር ሕዝቦችም የክብርና የኩራት ታሪካዊ መሠረት የጣሉበት የድል ታሪክ ነው።
ዛሬ በዚሁ ታሪካዊ ሥፍራ የአፍሪካ የፖለቲካ ኃይሎች መሰባሰባቸው፣ ያለፈውን የጋራ ድል በማስታወስ የአህጉሪቱን የጋራ ፈተናዎች በውይይት፣ በመግባባትና በትብብር ለመፍታት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል።
ይህም አዲስ አበባ የአፍሪካ የነፃነት ታሪክ መዲና ብቻ ሳትሆን፣ የፖለቲካ ውይይት፣ የአህጉራዊ መግባባት፣ የጋራ መፍትሄና የተባበረ የወደፊት ራዕይ ማዕከል መሆኗን የሚያረጋግጥ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።
ትናንት የተጀመረው 2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች አህጉራዊ ጉባኤ "ለዕድገት መምራት" በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ዛሬም ቀጥሎ ይካሄዳል።
በጉባኤው የገዢና ተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን፣ የሀገር መሪዎችን፣ ሚኒስትሮችን፣ ምሁራንና የሲቪል ማኅበራት ተወካዮችን ጨምሮ ከ1 ሺህ በላይ እንግዶች ከመላ አህጉሪቱ ተሳትፈዋል።