በክልሉ በመኸር ወቅት እስካሁን ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ የደረሰ ሰብል ተሰብስቧል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በመኸር ወቅት እስካሁን ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ የደረሰ ሰብል ተሰብስቧል
ባህርዳር፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በዘንድሮው የመኸር ወቅት ከለማው መሬት እስካሁን ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የደረሰ ሰብል ከብክነት በፀዳ መልኩ መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ አርሶ አደሩ የድህረ ምርት ብክነትን ሊቀንስ በሚያስችል መልኩ እንዲሰበስብ እየተደረገ ነው።
ለዚህም በ2018/19 የምርት ዘመን በክልሉ በመኸሩ ከለማው ከ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እስካሁን በተደረገ ጥረት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን ገልጸዋል።
ሰሊጥ፣ ገብስና ማሾ ሙሉ በሙሉ ተሰብስቦ መጠናቀቁን ገልጸው፣ ሌሎች የደረሱ እንደ በቆሎ፣ ጤፍ፣ የቅባትና የጥራጥሬ ሰብሎች ደግሞ በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።
አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመታደግ የድህረ ምርት ብክነትን በሚያስቀሩ የኮምባይነርና አነስተኛ የሰብል ማጨጃና መውቂያ መሳሪያዎች ታግዞ ምርቱን እንዲሰበስብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የቴክኖሎጂ አቅርቦት በሌለባቸው አካባቢዎች ደግሞ አርሶ አደሩ በደቦና በቤተሰብ ጉልበት በመጠቀም የምርት ብክነትን በሚቀንስ አግባብ ሰብስቦና ወቅቶ ወደ ጎተራ እንዲያስገባ ባለሙያዎች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አመልክተዋል።
ምርቱ ወደ ጎተራ ከገባ በኋላም በተባይና በነቀዝ እንዳይበላ ተባይን መከላከል በሚያስችሉ ሄርሜቲክ የሰብል ማከማቻ ጆንያዎችንና የብረት ጎተራዎችን መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል።
በመኸሩ ወቅት የለማው ሰብል ሙሉ በሙሉ ታጭዶና ተወቅቶ ሲጠናቀቅ ከ205 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዳይሬክተሩ አክለው አስታውቀዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ቀለብ እንግዳው ፣ በስምንት ሄክታር መሬት ያለሙትን የሰሊጥና ማሾ ሰብል አጭደውና ወቅተው መሰብሰባቸውን ተናግረዋል።
ያገኙትን 56 ኩንታል ምርት በቀጣይ ወደ ገበያ አቅርበው በተሻለ ዋጋ የመሸጥ እቅድ አላቸው።
በአንድ ሄክታር መሬት ያለሙትን የገብስ ሰብል ከብክነት በጸዳ መልኩ አጭደው መሰብሰባቸውን የገለጹት ደግሞ በደቡብ ጎንደር ዞን የእስቴ ወረዳ አርሶ አደር ልቅናው መንጌ ናቸው።
በጤፍና በሌሎች ሰብሎች አንድ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ማልማታቸውን ገልጸው በቀጣይ የሰው ጉልበትን በመጠቀም የምርት ብክነትን ሊቀንስ በሚችል መልኩ ለመሰብሰብ እንደተዘጋጁ ገልጸዋል።
በክልሉ በ2017/2018 የምርት ዘመን በመኸር ወቅት ከለማው መሬት ከ188 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።