ቀጥታ፡

ከማጃንግ ዞን ከ42 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ ነው

ጋምቤላ፤ ጥቅምት 27 /2019 (ኤዜአ)፦በጋምቤላ ክልል ከማጃንግ ዞን በበጀት አመቱ ከ42 ሺህ  ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን  የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ልማትና ግብይት ቡድን መሪ ሲሳይ በላይነህ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ የደረሰ የቡና ምርት እየተሰበሰበ ነው ።

እየተሰበሰበ ካለው ቡና 48ሺህ  896 ቶን ምርት ይገኛል ተብሎ  እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

በበጀት አመቱ ከሚጠበቀው አጠቃላይ ምርት ውስጥ ከ42 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ የታጠበና ያልታጠበ ቡና ለማእከላዊ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በበጀት አመቱ ከዞኑ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ቡና ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው ከዞን እስከ ቀበሌ የጥራትና የግብይት ቁጥጥር ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።




በዞኑ አሁን ላይ በአርሶ አደሮችና በባለሀብቶች ከለማው 71 ሺህ 680 ሄክታር በላይ ማሳ ላይ አብዛኛው ምርት መሰብሰቡን ጠቁመው በቀጣይ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለማእከላዊ ገበያ የማቅረብ ስራ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

በዞኑ በጎደሬ ወረዳ በቡና ልማት ከተሰማሩ አርሶ አደሮች መካከል አቶ አብዱ ሁሴን በሰጡት አስተያየት፣ በባለሙያ በሚሰጣቸው ድጋፍ በመታገዝ  ጥራቱን የጠበቀ ቡና እያዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።

በቡና ጥራትና ግብይት በግብረ ኃይሉ እየተሰጣቸው ያለውን ድጋፍ በመጠቀም የቡና ምርታቸውን በጥራት እየሰበሰቡ መሆኑን  የገለጹት ደግሞ አርሶ አደር  ይማም ሀጂ ናቸው።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም