ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ በፍራንስ 24 ዕይታ

ኢትዮጵያ የኮፕ32 (COP32) ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ በአፍሪካ የንጹህ ኢነርጂ መሪነቷን ለማረጋገጥ በመዘጋጀት ላይ ትገኛለች።
 
ሀገሪቱ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ በተጨማሪ በደቡብ ምዕራብ አገሪቱ በሚገኘው የኦሞ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኘው የኮይሻ ግዙፍ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በመገንባት ላይ ስትሆን፣ይህም የሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገር ለጎረቤት አገራት የሚደረገውን የኃይል ኤክስፖርት ለማሳደግ ያለመ ነው።
 
አዲሱ ግድብ በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱን 95 በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይል ከሚያመነጩት 16 ዋና ዋና የውሃ ኃይል ማመንጫዎች ጋር የሚቀላቀል ሲሆን፣ የኢትዮጵያን የኃይል ዋስትና የበለጠ ያጠናክራል።

ይህም ሀገሪቱ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ከማዋል ባለፈ ለጎረቤት አገራት የምታቀርበውን የንጹህ ኢነርጂ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ እንድታሳድግ የሚያስችል መሆኑን የፍራንስ 24 ጋዜጠኛ ቶም ካኔቲ ዘገባ ያመለክታል።


 

ግዙፍ የሆነ የውሃ ኃይል ማመንጨት አቅም አለን፤ ነገር ግን እስከ አሁን የተጠቀምንበት የሀብታችንን ጥቂት ድርሻ ብቻ ነው።ስለዚህ የተፈጥሮ ሀብታችንን በአግባቡ ለመጠቀም ጠንክረን መስራት ይኖርብናል  ይላሉ  የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፕሮጀክት ማናጀር  መብራቱ ተሾመ።
 
ኢትዮጵያ በውሃ ኃይል አጠቃቀሟ ምክንያት በአፍሪካ ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ካላቸው ሀገራት አንዷ ስትሆን፣ የአንድ ግለሰብ የካርቦን ልቀት መጠንም ከዓለም አቀፉ አማካይ በ97 በመቶ ያነሰ ነው።
 
የኮይሻ ግድብ ግንባታ ሌላኛው የኢትዮጵያ የንጹህ ኢነርጂ ዋና ማሳያ ነው።
 
የዊቢውልድ ፕሮጀክት ማናጀር ስቴፋኖ ሲልቪ የምንጠቀምበት ኃይል ራሱ ከ150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ካለው ሌላ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በተዘረጋ መስመር ነው የሚቀርበው ሲሉ ገልጸዋል።
 
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም የሀገሪቷን ፍትሃዊ የሀብት አጠቃቀም እና በጋራ የመልማት ጽኑ መሻት በግልጽ የሚያሳይ ነው።
 
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተባባሪ ፕሮፌሰር እና የውሃ ተመራማሪ ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) የግድቡ አላማ ውሃን አግዶ ማስቀረት ሳይሆን ውሃን በመጠበቅ ለኃይል ማመንጫነት ከተጠቀመ በኋላ ወደ ታችኛው ተፋሰስ እንዲፈስ የሚያደርግ  መሆኑን ገልጸዋል።
 
አክለውም  የግብፅ ምንጮችን ጨምሮ በተለያዩ አካላት እንደተረጋገጠው የወንዙ ፍሰት የቀጠለና ይበልጥ የጨመረ እንጂ በግድቡ ምክንያት የተከሰተ የውሃ እጥረት የለም ብለዋል።
 
እ.አ.አ በ2027 የኮፕ32 አየር ንብረት ጉባኤን የምታስተናግደው ኢትዮጵያ፣ መድረኩን በአህጉሪቱ የታዳሽ ኢነርጂ መሪነቷንና አቅራቢነቷን ይበልጥ ለማረጋገጥ ልትጠቀምበት ማቀዷን የፍራንስ 24 ዘገባ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም