ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ማማ፦ከራስ አልፎ ለቀጣናው የተሰጠ በረከት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ማማ፦ከራስ አልፎ ለቀጣናው የተሰጠ በረከት
ኢትዮጵያ ከተፈጥሮ የታደለችው ሰፊ የውኃ፣ የንፋስ፣ የፀሐይና የጂኦተርማል (የምድር ውስጥ እንፋሎት) ጸጋ የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማማ አድርጓታል።
ሀገሪቱ የምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ከንጹሕና ከአረንጓዴ ምንጮች የሚገኝ ነው።
ይህ ስትራቴጂያዊ የኃይል ልማት አቅጣጫ ሀገሪቱ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና በኢንዱስትሪ መስፋት ምክንያት የሚኖራትን ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት በራሷ አስተማማኝ አቅም እንድትሸፍን አስችሏታል።
የዚህ ታላቅ አቅም ዋነኛ ማሳያና ማዕዘን የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ነው።
ይህ ግዙፍ መሠረተ ልማት የሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን በከፍተኛ ደረጃ ካሳደገው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ስኬት ባሻገር፣ የኢትዮጵያን የምህንድስና ከፍታ ለዓለም ያሳየ ደማቅ አሻራ ነው።
በንጹሕ ኃይል ልማት ላይ የተደረገው ይህ ኢንቨስትመንት የካርቦን ልቀትን በመቀነስ ረገድ ዓለም አቀፋዊ ፋይዳው የጎላ ነው።
ይህ የንጹሕ ኃይል ማመንጨት አቅም ከራስ ፍጆታ አልፎ ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የተሰጠ ትልቅ በረከትና የትስስር መፍጠሪያ አቅም ሆኗል።
የኮይሻ የሃይል ማመንጫም የኢትዮጵያን የኢነርጂ አቅም የበለጠ የሚያሳድግ ነው።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ሃይል በማቅረብ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ ይህ ቀጣናዊ የኃይል ትስስር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ይገኛል።
ይህ የጎረቤት ሀገራትን የኃይል ፍላጎት ከማሟላት በላይ፣ ቀጣናውን በልማት ይበልጥ እያስተሳሰረ ነው።
ኢትዮጵያ ጎረቤቶቿን በንጹሕ ኃይልና በጋራ ልማት የምታስተሳስር፣ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ቀዳሚ ሀገር መሆኗን በተግባር አሳይታለች።
ይህ የታዳሽ ኃይል ልማት ስትራቴጂ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረት የሚደግፍና የቀጣናውን የኢኮኖሚ ትስስር የሚያፋጥን ዋነኛ ሞተር ነው።
ሀገሪቱ ወደፊትም ይህንን የንጹሕ ኃይል አቅርቦት ይበልጥ በማስፋት፣ ለምሥራቅ አፍሪካ ብልጽግና እና ለዘላቂ ልማት የማይናወጥ መሠረት ሆና ትቀጥላለች።