ቀጥታ፡

በመዲናዋ የሚካሄዱ መድረኮች የኢትዮጵያን የቱሪዝም መስህቦች ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል ፈጥረዋል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 26/2019 (ኢዜአ)፦በመዲናዋ የሚካሄዱ አህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችና የቱሪዝም መስህቦቿን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለፀ፡፡

የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር «አፍሪካ ሴሌብሬትስ 2026» ከህዳር 1 እስከ 6 ቀን 2019 ዓ.ም «አንድ አፍሪካ፤ አንድ ህዝብ፣ ባህላችንን፣ ፈጠራችንን እና ስራ ፈጣሪነታችንን ለአንድነታችን እና ለጋራ ብልጽግናችን ማስተባበር» በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አስታውቋል።

በቢሮው የቱሪዝም ዲጂታል ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬሕይወት ገብረመድኅን ፕሮግራሙን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ አዲስ አበባ አሁን ላይ ያለችበት ከፍተኛ የለውጥ ሂደት የዜጎቿን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ በዓለም አደባባይ ጎልታ እንድትታይ አድርጓታል።

በመሆኑም የአፍሪካ ሴሌብሬትስ 2026 ዝግጅት ኢትዮጵያ ያከናወነቻቸውን ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችና የቱሪዝም ስፍራዎች ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በማስተዋወቅ የከተማዋን መልካም ገጽታ ለመገንባት ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ለአፍሪካ ሴሌብሬትስ ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን የቱሪስት መዳረሻዎች የማስተዋወቅና የጉብኝት መርሃ ግብር በማዘጋጀት ከታሪክ፣ ከባህልና ከእሴት ጋር የማገናኘት ስራ በስፋት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

አክለውም ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ትስስር በመፍጠር የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት ከተማዋ ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንደሚሰራ ተናግረዋል።


 

የአፍሪካ ሴሌብሬትስ (Africa Celebrates) ፕሬዚዳንት ሌክሲ ሞጆ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ ሴሌብሬትስ ዋና ዓላማ በአህጉሪቱ የሚኖሩ አፍሪካውያንን በማቀራረብ፣ ወንድማማችነትን በማጠናከር በአጋርነት እና በአንድነት ለአፍሪካ ብልጽግና መስራት ነው ብለዋል።

ይህንን ዝግጅት ለማካሄድ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ተመራጭ መሆኗንም ገልጸዋል።


 

የአውሮፓ ህብረት ተወካይ ሪታ ፎርቱናቶ ባፕቲስታ፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ ደስታ እንደተሰማቸው በመግለጽ ለከተማዋ ያላቸውን ጥልቅ አድናቆት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም