ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የዲጂታል ሉዓላዊነት ገንቢ ሚና እየተወጣች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የዲጂታል ሉዓላዊነት ገንቢ ሚና እየተወጣች ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 26/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመጀመሪያውን የመደመር ሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ በመገንባት ለአሕጉሪቷ የዲጂታል ሉዓላዊነት ገንቢ ሚና እየተወጣች መሆኑን በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ረዳት አስተባባሪ መሃመድ እንድሪስ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ "ዕድገትን መምራት ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።
የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ አካል የሆነው የአፍሪካ ሴቶችና ወጣቶች የፖለቲካ አመራር ፎረም 2026 በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተካሄዷል።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ረዳት አስተባባሪ መሃመድ እንድሪስ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የዘመኑ ወጣቶች ቴክኖሎጂን የዕለት ተዕለት መደበኛ መገልገያቸው አድርገውታል።
ኢትዮጵያ በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የዜጎቿን ደህንነት ማረጋገጥ ችላለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ስኬታማና የብልፅግናዋ ፍኖተ ካርታ የሚሆን ሀገራዊ ምክክር በማድረግ ለብሔራዊ ደህንነቷ መሰረት መጣሏንም ገልጸዋል።
ቅቡልነት ያለው ተቋም ለብሔራዊ ደህንነትና ሉዓላዊነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ በማካሄድ አስተማማኝ ተቋማት እየገነባች መሆኑን ማሳየቷን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከተቋማት ግንባታ ባለፈ የዲጂታል ቴክኖሎጂ በመጠቀም አሰራሯን ማዘመን ጀምራለች ብለዋል።
በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እያንዳንዳቸው ከ200 በላይ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችሉ 70 ማዕከላት መገንባታቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ ማዕከላት የበለጸጉት፣ የሚተዳደሩት፣ ቁጥጥር የሚደረግባቸው በኢትዮጵያውያን መሆኑን ገልጸው፤ ለዲጂታል ሉዓላዊነት መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ደህንነቷ የተረጋገጠና የተረጋጋች አፍሪካን እውን ለማድረግ የዲጂታል ሉዓላዊነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል በራሷ የሚተዳደር ቴክኖሎጂ መገንባት አለባት ብለዋል።
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ወጣቶችን ከሰው ሰራሽ አስተውሎት ጋር በተያያዘ በቂ ግንዛቤ መፍጠር መቻሏን ገልጸዋል።
መንግሥት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የተቋማት አወቃቀር በቴክኖሎጂ የዳበረ መሆኑን ተናግረዋል።
በመደመር እሳቤ የምትመራው ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመጀመሪያውን የመደመር ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዩኒቨርሲቲ በመገንባት ለአሕጉሪቷ የዲጂታል ሉዓላዊነት ገንቢ ሚና እየተወጣች ነው ብለዋል።
የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የሰላም ወጣቶች አምባሳደር አሚና ቤሎ በበኩላቸው፤ ቴክኖሎጂ በተረዳነው ልክ የሚያገለግል የዕድገት አልያም የውድመት መንስኤ መሆኑን ገልጸዋል።
ስለሆነም የአፍሪካን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሰው ሰራሽ አስተውሎትና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ወጣቶችን በበቂ ደረጃ ማስገንዘብ ይገባል ብለዋል።
ዲጂታል ቴክኖሎጂ የሰላምና ደህንነት፣ የልማትና ብልፅግና መሰረት መሆኑን ጠቅሰው፤ ተጠያቂነት ያለበት፣ ብቁና ግልጽ የመንግሥት አሰራር ለማንበር እንደሚያግዝ አብራርተዋል።
ስለሆነም ዲጂታል ቴክኖሎጂ ቅንጦት ሳይሆን ወሳኝ የትኩረት መስክ መሆኑን ገልጸው፤ የዜጎችን መረጃ ለመጠበቅ ዲጂታል ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂን ለማስተዳደር ወጣቶች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው በማንሳት፤ ከአፍሪካ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ ቴክኖሎጂ ማበልጸግ እንደሚገባ ገልጸዋል።