ቀጥታ፡

በክልሉ የግብርና ኤክስፖርት ምርቶች እና የሌማት ትሩፋት ውጤታማነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ

ቦንጋ፤ ጥቅምት 26/2019 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የግብርና ኤክስፖርት ምርቶች እና የሌማት ትሩፋት ውጤታማነትን ለማሳደግ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ በንቅናቄ ለሚመሩ የግብርና ልማት ሥራዎች ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባም ተመላክቷል።

"ምርታማነትን ማረጋገጥ ለክልላችን ማንሰራራትና ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ በቦንጋ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የክልሉ የግብርና ልማት ሥራዎች የንቅናቄ መድረክ ተጠናቋል። 


 

በመድረኩ የበጋ መስኖ ስንዴ፣ መደበኛ መስኖ፣ የበልግ አዝመራ፣ የሌማት ትሩፋት እንዲሁም የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ልማትን በተመለከተ የንቅናቄ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን የጋራ አቅጣጫም ተቀምጧል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ የግብርና ሥራዎችን በውጤታማነት መምራት ግንባር ቀደም አጀንዳ መሆን አለበት።

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በክልሉ ከተተገበረ በኋላ የእንስሳት ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶና አርብቶ አደሩን የአመጋገብ ሥርዓት ከማሻሻል ባለፈ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱ እያደገ መምጣቱን ገልፀዋል።

በክልሉ ቀጣይነት ያለው የግብርና ምርታማነትን ለማረጋገጥ በሌማት ትሩፋት የተደራጁ መንደሮችን ማጠናከር እና የእንስሳት መኖ አጠቃቀምን ማሻሻል ትኩረት የተሰጠው መሆኑንም አቶ ማስረሻ አመልክተዋል።

በክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ልማት ለበርካቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የብዙዎች የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆናቸው ለልማቱ መስፋፋትና ለጥራት ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


 

ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ የግብርና ሥራዎችን አመራሩ በግንባር ቀደምነት ሊያሳካ ይገባል ያሉት ደግሞ የክልሉ የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራ ናቸው፡፡

ምርትን በማሳደግ ገበያን ማረጋጋትና የግብርና ሥራዎችን ለሥራ ዕድል ፈጠራ በስፋት መጠቀም ይገባል ብለዋል። 

በንቅናቄ ለሚመሩ የግብርና ሥራዎች ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የሕዝቡን ተጠቃሚነት በተጨባጭ ማሳደግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። 


 

የመድረኩ ተሳታፊዎችም በዞናቸው የግብርና ስራዎችን በተለየ መልኩ በመደገፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በመድረኩ በሌማት ትሩፋት፣ በኤክስፖርት ምርቶች እንዲሁም በመስኖ ልማት ሥራዎች በቀጣይ ለማከናወን በተቀመጠ አቅጣጫ መሰረት ሰርቶ ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም