ቀጥታ፡

የፖለቲካ አመራሮች ወታደራዊ ስልጠና መውሰዳቸው የአመራር ብቃትን ያጎለብታል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 26/2019 (ኢዜአ) ፦ የፖለቲካ አመራሮች የወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ ስልጠና መውሰዳቸው የአመራር ብቃትን ያጎለብታል ሲሉ የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ይመር መኮነን ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በሁርሶ ዕጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሲወስዱት የቆየው የወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ ስልጠና ተጠናቋል፡፡

በሥልጠናው ማጠቃለያ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ይመር መኮነን እንደገለጹት የከፍተኛ አመራሮች የወታደራዊ ሳይንስ ጥበብን መማርና መሠልጠን የመከላከያ ሠራዊቱን የሥራ ባህል፣ ዲሲፕሊን እና መርሆዎች እንዲያውቁ የሚያግዝ ነው።

ሥልጠናው ከአካላዊና አእምሯዊ ዝግጁነት ከቡድን ሥራ እንዲሁም ከስትራቴጂካዊ አመራር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ተግባራዊና ንድፈ ሃሳባዊ እውቀትን ለማዳበር ያለመ መሆኑን ገልጸው በሲቪል አመራርና በመከላከያ ተቋም መካከል የጋራ ግንዛቤን ለማጠናከር እንደሚያግዝም አመላክተዋል፡፡

ከፍተኛ አመራሮቹ የወታደራዊ ሳይንስ ስልጠና መውሰዳቸው ሀገርን ወደ ተሻለ የዕድገት ጎደና ለማሻገር የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

ከነበራቸው የሥራ ባህል በተጨማሪ የወታደራዊ የሥራ ባህልና ሀገር ወዳድነትን እንዲሁም እየሞቱ ሀገርን የማፅናት የውትድርና ሙያን ለመገንዘብ እንደሚረዳም አንስተዋል።

አመራሮቹ በስልጠናው ያገኙት ተሞክሮ የመከላከያ ሠራዊቱን ተግባርና ኃላፊነት በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት እንዲሁም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተቀናጀ አመራር ለማጠናከር እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡

በሁርሶ የዕጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለከፍተኛ የሀገሪቱ አመራሮች የተሰጠው ስልጠና የተቋሙን የማሠልጠን አቅምና ልምድ ያሳየ ተሞክሮ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡


 

የከፍተኛ አመራሮች ሥልጠና ወታደራዊ እውቀትን፣ የአመራር ብቃትንና የሀገራዊ ርዕይ ትስስርን ለማጉላት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡

የሥልጠናውን ሪፖርት ያቀረቡት የሁርሶ ዕጩ መኮንኖች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል ከድር ጫጮ በበኩላቸው ከፍተኛ አመራሮቹ በተግባርና በንድፈ ሃሳብ የተከታተሉትን ስልጠና የሲቪል አመራሩ እና መከላከያ በጋራ የሀገርን ርዕይ ማሳካት የሚችሉበት ነው ብለዋል፡፡

ስልጠናው የሃገርን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅና የደህንነት ጉዳዮችን በተቀናጀ አመራር ለመምራት የሚያስችል የጋራ ግንዛቤ የፈጠረ ነው ማለታቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም