ቀጥታ፡

የሲዳማ ክልልን የኢኮኖሚ ጸጋዎች አቀናጅቶ በመጠቀም የሕዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

ዳዬ፤ ጥቅምት 26/2019 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል ያሉ የኢኮኖሚ አቅሞችና ጸጋዎችን አቀናጅቶ ጥቅም ላይ በማዋል የሕዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ  በቅንጅት እንደሚሠራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መሳይ ኃይሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመደመር መንግሥት የተያዙ የልማት እቅዶችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ከምሥራቃዊ ሲዳማ ዞን ነዋሪዎች ጋር ዛሬ በዳዬ ከተማ ተወያይተዋል።


 

‎ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት ክልሉ ወደ ኢኮኖሚ ተቀይረው በአግባቡ ከተመሩ ትልቅ አቅም ሊሆኑ የሚችሉ የተፈጥሮ ሀብቶችና የሰው ሀይል አለው።

‎በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና በሌሎች የኢኮኖሚ መስኮች ያሉ ሀብቶችን ከሰው ኃይል አቅም ጋር በማቀናጀት የክልሉን ዜጎች የልማት ተጠቃሚነት ፍላጎት ለማሟላት እንደሚሰራም ገልፀዋል።

‎በመሠረተ ልማት የክልሉን ዜጎች ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹት መሳይ (ዶ/ር)፣ በዚህም የህዝብ የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እንደሚፈቱ አረጋግጠዋል።

‎ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር ውጤታማ እንዲሆኑና የተሻለ ሀብት መፍጠር እንዲችሉ የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወኑም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።


 

በተለይ ብቁ፣ ተወዳዳሪና በራሳቸው ሥራን መፍጠር እንዲችሉ አስፈላጊ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸው፣ በየደረጃው ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ከህዝብ ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

‎የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋና በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ የተገልጋዮችን እርካታ ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱንም አመልክተዋል።

‎በዞኑ ከተለያዩ ወረዳና ከተሞች የተውጣጡ የውይይቱ ተሳታፊዎች መንግስት ህዝብን በልማትና በመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ ለማድረግ ላከናወናቸው ተግባራት አመስግነው፣ አሁንም ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎች እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል።


 

‎የዳኤላ ወረዳ ነዋሪ አቶ ዮሐንስ ቦርጬ፤ የመደመር መንግሥት የህዝብን ፍላጎት ቀርቦ ለማዳመጥና ችግሮቹን ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

‎በወረዳው በእርሻ ሥራና በእንስሳት ልማት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች የሚበረታቱ ቢሆንም ከመሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል።

‎ለአብነት በወረዳው ያለው የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻ መሆኑን ነዋሪው አንስተዋል።


 

‎የጭሬ ወረዳ ነዋሪ አቶ አርጋታ አያኔ በበኩላቸው፤ መንግሥት የጀመራቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ከዳር እንዲደርሱ የበኩላቸውን ለመወጣት ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።

‎ምርታችንን ወደ ገበያ ለመውሰድ እንዲሁም ማህበራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ መንገድ ትልቅ ሚና አለው ያሉት አቶ አርጋታ፣ በአካባቢያቸው ግንባታው ለተጓተተው የአስፋልት መንገድ የክልሉ መንግሥት አፋጣኝ እልባት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

‎የመድረኩ ተሳታፊዎች ከኤሌክትሪክ ሀይል፣ ከቴሌኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማት፣ ከጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ጋር በተያያዘ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱላቸውም ጠይቀዋል።

በውይይት መድረኩ የክልሉ አመራሮች፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም