የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በባህር፣ በአየርና በየብስ ግዳጅን ለመፈፀም በሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በባህር፣ በአየርና በየብስ ግዳጅን ለመፈፀም በሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/ 2019 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በባህር፣ በአየርና በየብስ ግዳጅን ለመፈፀም በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ የባህር ኃይል አባላትና አመራሮች ገለጹ።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚገኙ ክፍሎች በቀጣናው ሊከሰቱ የሚችሉ ማናቸውንም ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለማጥፋት አስተማማኝ የተቀናጀ ግዳጅ እየፈፀሙ ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ ባህር ኃይል ሚዲያ ኃላፊ ኮማንደር ካሳሁን ኪዳኔ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የባህር በሯን ብቻ ሳይሆን የባህር ኃይሏንም ጭምር ያለአግባብ አጥታ ቆይታለች።
ከመከላከያ ሰራዊት ሪፎርም ወዲህ የባህር ኃይሉ እንደ አዲስ ተደራጅቶ በባህር፣ በአየርና በየብስ የተሟላ ግዳጅን መወጣት የሚችል ኃይል ፈጥሯል ብለዋል።
በሁሉም የባህር ኃይል ቀጣናዎች የሚገኙ አመራርና አባላት ዓለም አቀፍ ህግን በተከተለ ሁኔታ የባህር ላይ ፍለጋና ነፍስ ማዳን ግዳጆችን በቁርጠኝነት ለመወጣት በአስተማማኝ ቁመና ላይ እንደሚገኙም ገልፀዋል።
የባህር ኃይሉ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት ለመፈጸም የሚያስችል የአካልም ሆነ የስነ ልቦና ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
የተቀናጀ የባህር፣ የአየርና የየብስ ስልጠናው ነገ ወደ ባህር በራችን ስንመለስ የባህር ላይ ፍለጋና ማዳን ስራን ታሳቢ ያደረገ ነው ሲሉም መናገራቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ መረጃ ያመለክታል።