ቀጥታ፡

የአፍሪካ ወጣቶች የአሕጉራቸውን መፃኢ ጊዜ የሚቀርጹ መሀንዲሶች ናቸው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 26/2019 (ኢዜአ)፦የአፍሪካ ወጣቶች የአሕጉራቸውን መፃኢ ጊዜ የሚቀርጹ መሀንዲሶች መሆናቸውን የአፍሪካ ወጣቶች በፖለቲካ ፎረም የፓናል ውይይት አቅራቢዎች ገለጹ።

የትልቅ ሀገር ትልቅ ሕዝብ እና ታላቅ ርዕይ የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ አካል የሆነው የአፍሪካ ሴቶችና ወጣቶች የፖለቲካ አመራር ፎረም 2026 በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው። 

የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ "ዕድገትን መምራት ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" የሚለው መሪ ሀሳብ ከአፍሪካ ወቅታዊ የትኩረት አጀንዳ ጋር የተጣጣመ መሆኑ ተመላክቷል። 

የካሜሩን ብሔራዊ ወጣቶች መሪና የፎረሙ ሊቀ መንበር ቤንጃሚን ፍሩ ኒዲ በዚህ ወቅት እንዳሉት አፍሪካ የወጣቶች አሕጉር ናት። 

በአፍሪካ እምቅ የተፈጥሮ ሀብትና ጸጋ እንዳለ ገልጸው፤ በማዕድን፣ በግብርና እና በሌሎችም ጸጋዎቿ ለወጣቶች አስተማማኝ የሥራ ዕድል መፍጠር አለባት ብለዋል። 

አሕጉሪቱ የምሁራን፣ የልሂቃን፣ ምጡቅ አዕምሮ ያላቸው ወጣቶች ምድር ናት ያሉት ሊቀ መንበሩ፤ የወጣቶችን አቅም ለቀጣይ መሪዎች መነሻ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል። 

ወጣቶችን ወደ ልማትና ብልፅግና መንገድ ለመምራት ለዜጎች ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚገባ አንስተው፤ ለዚህ ደግሞ ሁሉም አካል አበርክቶ ሊኖረው እንደሚገባ ገልጸዋል። 


 

የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር ነብዩ ስሑል በበኩላቸው፤ የወጣቶችን ተሳትፎ በማጎልበት ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ነገን ማውረስ የሁሉም ሀላፊነት ነው ብለዋል። 

ኢትዮጵያ በብልፅግና ፓርቲ መሪነት ሀገር በቀል በሆነው የመደመር ፍልስፍና ትውልድ ተሻጋሪ አጀንዳዎችን መቅረጿን ተናግረዋል። 

በዚህም ፓርቲው ትልልቅ ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸው፤ ይህም ብሔራዊ ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማትን እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል። 

የመደመር ፍልስፍና ሁሉም አስተዋፅኦ እንዲኖራቸው የሚጋብዝ የወጣቶች ውርስ መሆኑን በማውሳት፤ ለዘላቂ ሰላምና  ልማት ወሳኝ የትውልድ አደራ ነው ብለዋል። 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተዘጋጀው የመደመር ትውልድ መፅሀፍ ትውልድ ተሻጋሪና የተሻለ ነገን መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። 

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የቀድሞው የወጣቶችና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ዩቪስ ቡንኩሉ፤  የወጣቶች የቅድሚያ ትኩረት በሀገራቸው ጉዳይ የሚሳተፉበት መድረክ መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል። 

ይህ ደግሞ የሁሉንም ውሳኔ ሰጭዎች ሀላፊነትና የተግባር ርምጃ ይጠይቃል ብለዋል። 


 

በኢትዮጵያ የሲሸልስ ኤምባሲ ምክትል ጸሀፊ ሺሻ ሀሮ፤ ለወጣቶች የነቃ ተሳትፎና አካታችነት የኢኮኖሚ ብዝሀነት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። 

አፍሪካ ያላትን እምቅ ጸጋ በአግባቡ በመጠቀም የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል። 

የዩጋንዳ ፕሬዝዳንት የወጣቶች ጉዳይ ልዩ ረዳት ዳንኤል ኦባል፤ ዓድዋ የአፍሪካውያን የህልውና ምልክት የለውጥ አብነት መሆኑን ገልጸዋል። 


 

አፍሪካ ሀገራቸው፤ ዩጋንዳ ደግሞ ሰፈራቸው መሆኑን ገልጸው፤ በአፍሪካ ያለው አቅም ወደ ስራ ዕድል ካልተቀየረ ውድቀትን ያመጣል ብለዋል። 

በታንዛኒያ የቻማ ቻ ሞፒንዱዚ ፓርቲ የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዋና ጸሀፊ ፓስካል ማሳሎ በበኩላቸው፤ ያለ ወጣቶች ተሳትፎ የሚሳካ ግብ የለም ብለዋል። 


 

በመሆኑም ወጣቶችን ያሳተፈና በፍትሐዊነት ያካተተ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም