ቀጥታ፡

የድሬ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች እያቀላጠፈ ነው

ድሬዳዋ፣ ጥቅምት 26/2019 (ኢዜአ)-የድሬ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች እያቀላጠፈ መሆኑ ተገለጸ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ ማዕከሉ ቀደም ሲል በነበሩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ይስተዋሉ የነበሩ የአሰራር ጉድለቶችን ፈትቷል።


 

በተጨማሪም ሌብነትንና ወገንተኝነትን ለማስቀረት እንዲሁም የተገልጋይን ጊዜና ጉልበት ለመቆጠብ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው የገለጹት።

አስተያየታቸውን ከሰጡ የማዕከሉ ተገልጋዮች መካከል አቶ መለሰ ኬኔ እና አቶ ዘይኑ ሱልጣን በሰጡት ምስክርነት፤ ማዕከሉ ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ የተንዛዙ የመንግስት አሰራሮችን በአስደናቂ ሁኔታ መቀየር መቻሉን ተናግረዋል።


 

በተለይም ቀደም ሲል እንደ መሬት እና የመንጃ ፈቃድ ጉዳዮችን ለማስፈጸም በየቢሮው በመንከራተት እስከ ሦስት ወራት ድረስ ይፈጅ የነበረን ጊዜ በማስቀረት የጊዜ ብክነትን ማስቀረቱን አስረድተዋል።

ማዕከሉ ሥራ መጀመሩ ጉዳያቸውን በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ ለመጨረስ እንዳስቻላቸው የጠቀሱት ነዋሪዎቹ፤ ድሬ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሌብነትንና ወገንተኝነትን በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል፡፡


 

ወይዘሮ ወይንሸት ታምራት እና  አሸከርካሪው ወጣት ሚኪያስ ካሳዬ በበኩላቸው በማዕከሉ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በሁሉም የከተማው አቅጣጫዎች በማስፋፋት የህዝብን የአገልግሎት ጥያቄዎች ይበልጥ መፍታት ይገባል ብለዋል።


 

የድሬ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቀልጣፋ አሰራር የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ለማቀላጠፍ ማስቻሉንም ተናግረዋል።

የድሬ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና አስተባባሪ አቶ አወቀ ለገሰ በበኩላቸው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በማዕከሉ በ15 የአስተዳደሩ እና የፌደራል ተቋማት 103 መንግስታዊ አገልግሎቶች እየተሰጡ ነው።


 

ማዕከሉ ፈጣን የዲጂታል አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ስኬት እያስመዘገበ መሆኑንም ጠቁመዋል።

 የማዕከሉን የአገልግሎት አሰጣጥ በየጊዜው በመፈተሽ ውጤታማነቱን ይበልጥ ለማሳደግ በተደረገ የተገልጋይ እርካታ ጥናት ከ99 በመቶ በላይ የሚሆኑ ተገልጋዮች በማዕከሉ አሰራር መርካታቸውን በጥናቱ ተረጋግጧል ብለዋል።

ዋና አስተባባሪው አክለውም፣ አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ በድሬደዋ ለገሀሬ እና ሳቢያን ወረዳዎች አዳዲስ ቅርንጫፎች እየተገነቡ መሆናቸውንና ግንባታዎቹ በቅርቡ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁም አስታውቀዋል። 

ማዕከሉ የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ከማቀላጠፍ ባለፈ ዘመኑን የሚመጥን በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት መስጠቱን እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም