ቀጥታ፡

ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ የእንሰት ሰብል ሚናን በሳይንሳዊ መንገድ ለማላቅ የከፍተኛ ተምህርት ተቋማት ድርሻ መጉላት አለበት

አርባ ምንጭ፣ጥቅምት 26/2019 (ኢዜአ)፡-ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ የእንሰት ሰብል ሚናን በሳይንሳዊ መንገድ በማላቅ አበርክቶውን ለማሳደግ በሚከናወኑ ተግባራት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድርሻ መጉላት እንዳለበት ተገለጸ።

3ኛው ዓለም አቀፍ የእንሰት አውደ ጥናት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።


 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አብደላ ከማል (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ የእንሰት ሰብል ያለውን ሚና በሳይንሳዊ መንገድ በማላቅ በኩል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድርሻ መጉላት እንዳለበት ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው በእንሰት ሰብል ላይ ባከናወናቸው ምርምሮች እንሰት ለምግብ ዋስትና፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለኢንዱስትሪ ልማትና ለአገራዊ ኢኮኖሚ እድገት ያለው ሚና እንዲጎለብት ማስቻሉን ገልጸዋል።

ይህም እንሰትን ከባህላዊ አመራረት ወደ ሳይንሳዊ ምርምር፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂና የገበያ ተወዳዳሪነት ለማሸጋገር ጉልህ እርምጃ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው በባህላዊ መንገድ የሚከናወነውን እንሰት የማቀነባበር ሥራ ለማዘመን የእንሰት መከስከሻና መፋቂያን ጨምሮ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ማበልጸጉን አብደላ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ይህም በሴቶች ላይ ያለውን የሥራ ጫና በመቀነስ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ እንዲሁም የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የማይተካ ሚና ስላለው  የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።


 

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕሬዚዳንት ተክሉ ወጋየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት የእንሰት ሰብል ድርቅን ለመቋቋምና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ጉልህ ፋይዳ አለው።

በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የእንሰት ሰብል ተጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሳይንሳዊ መንገድ የእንሰት ሰብል ሚናን በማላቅ ጠቀሜታውን ለማሳደግ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሳይንሳዊ ምርምር የእንሰት ሰብል ሚናን ለማጎልበት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድርሻ ወሳኝ መሆኑን አንስተው፣ የሚከናወኑ ሳይንሳዊ ጥናቶችና ምርምሮች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ መንግስት የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባከናወነው የእንሰት ሰብል ጥናትና ምርምር በአምስት ክልሎች ከ4ሺህ በላይ አባላት ያሏቸው 48 ኢንተርፕራይዞች ወደ ሥራ መግባታቸውንና 32 ሺህ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የዘርፉ ተመራማሪና መምህር አዲሱ ፈቃዱ (ዶ/ር) ናቸው።


 

ተመራማሪና መምህሩ አንዳሉት የእንሰት ሰብል መስፋፋት በተኪ ምርት ከፍተኛ ድርሻ ከማበርከቱም በላይ የሀገሪቱን የምግብ ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ደረጃ ለማረጋገጥ ፋይዳው የላቀ ነው።

ሀገር በቀል የሆነውን የእንሰት ሰብል ሚናን ለማጎልበት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቤት ሥራ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ሰሞኑን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና ከፍተኛ ሳይንቲስት አዲሱ ፍቃዱ (ዶ/ር) በዘርፉ ላበረከቱት አስተዋጽኦ  የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (FAO) የ2026 የላቀ ስኬት ተሸላሚ መሆናቸው የሚታወስ ነው።

ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው አውደ ጥናት ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት የተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራማሪዎች እየተሳተፉ ሲሆን የተመረጡ 14 ጥናቶች ቀርበው ጥልቅ ውይይት እንደሚደረግባቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም