የጤና አገልግሎትን በፍትሐዊነት ተደራሽ በማድረግ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
የጤና አገልግሎትን በፍትሐዊነት ተደራሽ በማድረግ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ
ሆሳዕና ፤ጥቅምት 26/2019 (ኢዜአ) ፡- የጤና አገልግሎትን በፍትሀዊነት ተደራሽ በማድረግ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
የጤና ሚኒስቴርና የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎች የጤና ሴክተር የጋራ ግምገማ መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።
በወቅቱም ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እንደገለፁት፤ የጤና አገልግሎትን በፍትሐዊነት ተደራሽ በማድረግ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ።
የ2019 በጀት ዓመት ከሕዝብ ትልቅ አደራ የተቀበልንበትና የኅብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በከፍተኛ ትጋትና ቁርጠኝነት የምንሠራበት ወቅት ነው ብለዋል።
በተለይም በጤናው ዘርፍ በሚሰጡ አገልግሎቶች የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመለየት፣ አገልግሎቱ ከትውውቅና ከሌሎች አሠራሮች በጸዳ መልኩ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የሚደረግበትን ሥርዓት መፍጠር አንዱና ዋነኛው መሆኑን ተናግረዋል።
አገልግሎት ተቀባዩ ኅብረተሰብ በተገቢው መንገድ የሚስተናገድበትን ሥርዓት የማጠናከር ጉዳይ በልዩ ትኩረት ሊመራ እንደሚገባውም አሳስበዋል።
የውይይት መድረኩ በጤናው ዘርፍ የተገኙ ስኬቶችን ለማጠናከር፣ የተስተዋሉ ማነቆዎችን በመለየት ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥና ተግባቦት ለመፍጠር ያለመ መሆኑን አንስተዋል።
በዘርፉ በሕዝቡ ተቀባይነት ያለው የጤና አገልግሎት ሥርዓትን በመገንባትና ትውልድ ተሻጋሪ የጤና ሲስተምን በማጎልበት ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ የአመራሩ ቅንጅታዊ ትግበራ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምና የመደመር መንግሥት የጤና ስትራቴጂ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ቀጣይ አቅጣጫ እንደሚሰጥበትም ተመልክቷል።
በመርሐ ግብሩም የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልሎች ጤና ቢሮ ኃላፊዎችና የተጠሪ ተቋማት ዳይሬክተሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።