ገመሪ ሐይቅ-የበረሐው ልምላሜ ተስፋ - ኢዜአ አማርኛ
ገመሪ ሐይቅ-የበረሐው ልምላሜ ተስፋ
በሰለሞን ብርሃኑ (ሰመራ ኢዜአ ቅርንጫፍ)
ከሸዋ ኮረብታዎች፣ ከአምቦ ዙሪያ ተነስቶ ወደ ምሥራቅ የሚገሰግሰው ታላቁ አዋሽ ወንዝ፣ በመንገዱ ሸለቆዎችንና ሜዳዎችን፣ የእርሻ ማሳዎችንና የአርብቶ አደር መስኮችን አቋርጦ ከ1,200 ኪሎ ሜትር በላይ ይጓዛል። ከኢትዮጵያ ወንዞች መካከል የአዋሽ ዕጣ ፈንታ ለየት ያለ ነው፤ በአፋር ሞቃታማ ምድረ በዳ ውስጥ በሚገኙ ሐይቆች ውስጥ ገብቶ ይቀራል። ከእነዚህ የመጨረሻ መዳረሻዎቹ አንደኛው የገመሪ ሐይቅ ነው።
ሐይቁ የሚገኘው በአፋር ክልል፣ አውሲ ረሱ ዞን፣ አፋምቦ ወረዳ ነው። ከአይሳኢታ ከተማ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲሆን፣ ከጂቡቲ ድንበር ጥቂት የቀረበ ነው። የአፋምቦ ሐይቅና ከጂቡቲ ጋር የሚዋሰነው ዝነኛው የአቤ ሐይቅ ያዋስኑታል። የአቤ ሐይቅ ከሰማይ ጫፍ የሚወጡ የድንጋይ ጭስ ማውጫዎች የሚመስሉ ምሰሶዎቹ ይታወቃል። ገመሪም ከነዚህ የሐይቆች ሰንሰለት መካከል የሚገኝ የጠረፍ ጌጥ ነው።
70 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ባለ ግርማ ሞገሱ ሐይቅ፣ በአንድ በኩል አዋሽ የሚያመጣው ውሃ የሚያርፍበት ዕቃ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሕይወት ምንጭ ነው። ትኩረት ተሰጥቶት ቢሠራበት የመልማት ከፍተኛ አቅም እንዳለው ይታመናል፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የልማት አጋርነቱን ማሳየት ጀምሯል።
ምድረ በዳ በሚመስል ሥፍራ ላይ በሚገኘው በዚህ ሐይቅ ውስጥ አምባዛ፣ ቆሮሶና ቢቻ የተባሉ ሦስት የዓሣ ዝርያዎች ይኖራሉ። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአማካይ በዓመት 629 ቶን ዓሣ ለማምረት የሚያስችል አቅምም አለው። ይህ ቁጥር ለአንድ አርብቶ አደር አካባቢ ትልቅ የምግብና የገቢ ምንጭ ሊሆን የሚችል ነው።
ዓሣ የመመገብ ልማድ በአፋር አርብቶ አደር ማኅበረሰብ ዘንድ በታሪክ የተለመደ ባይሆንም፣ በማኅበር ተደራጅተው ወደ ዓሣ ማጥመድ የገቡ ወጣቶች ይህንን እየለወጡ ነው። ዓሣን ለገበያ በማቅረብ ከመጠቀማቸው ባሻገር፣ በአካባቢው አዲስ የምግብ ባሕል እንዲጎለብት እያደረጉ ነው።
ሐይቁ ለረጅም ዓመታት ጥቅም ላይ ሳይውል ቆይቷል። ለአርብቶ አደሩ ወደ ሌላኛው ስፍራ ለመሻገር የሐይቁን ዳርቻ በውሃ እያቋረጠ መሄድ የዕለት ተዕለት ፈተና ነበር። አሁን ግን የተገነባው መንገድ፣ የተሟላው መሠረተ ልማትና የተሠራው ድልድይ እንቅስቃሴውን ቀላል አድርጎለታል።
ይበልጥ ትልቅ ዕድል የፈጠረለት ደግሞ ወደ ጂቡቲ ወደብ የሚወስደው የአስፋልት መንገድ ከሐይቁ አጠገብ ማለፉ ነው። የጂቡቲ ወደብ ለኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ዋነኛ መተላለፊያ በመሆኑ፣ በዚህ መንገድ በየቀኑ የሚተላለፉ ተሽከርካሪዎች የዚህን ሐይቅ ዳርቻ ያልፋሉ። ቀደም ሲል በትራንስፖርት ችግር የተገለለው ስፍራ አሁን ከብሔራዊ የንግድ መስመር ጋር ተቆራኝቷል።
ሌላው ተስፋ ደግሞ የሐይቁ ውሃ ነው። በውሃ ፓምፕ በመጠቀም ወደ እርሻ ማሳዎች በማምጣትና ለመስኖ ልማት ማዋል ቢቻል፣ በበረሃማ ምድር አረንጓዴ ማሳዎችን መፍጠር ይቻላል።
ገመሪ ለቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከት ይችላል። አፋር ራሱ የዓለም የጂኦሎጂ ድንቅ ሥፍራ ነው፤ የዳናኪል ሸለቆ፣ የዳሎል ባለቀለም ምድር፣ የኤርታ አሌ እሳተ ገሞራና የሰው ዘር አመጣጥን የሚያሳዩ የቅሪተ አካል ግኝቶች የሚገኙበት ክልል ነው። በዚህ ጉዞ ውስጥ ገመሪን በጎብኚው መስመር ላይ ማካተት የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጎብኚዎችን ቁጥር ሊጨምር ይችላል።
ሐይቁን ከሁሉም ዳርቻዎች ሆኖ መመልከት መቻሉ ትልቅ ጥቅም ነው፤ ሆኖም የተሻለው ዕይታ የሚገኝበትን ቦታ መለየትና ማልማት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው። ዳርቻዎቹን በማልማትና በማስዋብ ለመዝናኛነት ማዋል ከተቻለ የገቢ ምንጭም ይሆናል።
በሐይቁ ውስጥ ራሱ በርካታ አዞዎች፣ ጉማሬዎችና የተለያዩ አዕዋፍት ይኖራሉ። በቅርብም በርቀትም ሊታዩ የሚችሉ ሲሆን ለጎብኚዎች ማራኪና ሳቢ ናቸው። አስገራሚው ነገር አዞዎቹ ተላምደው የሚኖሩ መሆናቸው ነው፤ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚናገሩት ለዘመናት ከአርብቶ አደሮችና ከእንስሳቶቻቸው ጋር ያለምንም ትንኮሳ ዘልቀዋል።
ሐይቁ የተፈጥሮ ውበት ብቻ ሳይሆን የታሪክ ምስክርም ነው። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ ግዛታቸውን እያሰፉ እስከዚህ ድረስ መጥተው የሰፈሩ ቅኝ ገዢዎች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ አልገዛም በማለቱና ኢትዮጵያዊነቱን በማስቀደሙ በሐይቁ ዙሪያ እስር ቤት ከፍተው ያሰቃዩ ነበር። ይህ ስፍራ ዛሬ የልማት ተስፋ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያዊነት ጽናት የታየበት ዳርቻም ነው።
በዚህ በረሃማ ስፍራ ውስጥ ለሕይወትና ለኑሮ መሠረት ሊሆን የሚችል ሐይቅ ተንጣሎ ይታያል። ሆኖም ውበቱና መስህቡ በአቧራ ተሸፍኖ፣ መልማት የሚገባውን ያህል ሳይለማ ቆይቷል። ይህንን የተጋረደ ኃይል ለመግለጥ እዚህም እዚያም የተጀመሩ የልማት ሥራዎች፣ ሕዝብን ማዕከል ባደረገና ተጠቃሚነቱን ባላቀ መልኩ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።