ኢትዮጵያ በሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ሚና ለአፍሪካና ዓለም ሀገራት ተምሳሌታዊ እርምጃ ወስዳለች - ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ሚና ለአፍሪካና ዓለም ሀገራት ተምሳሌታዊ እርምጃ ወስዳለች - ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ሚና ለአፍሪካና ዓለም ሀገራት ተምሳሌታዊ እርምጃ መውሰዷን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።
2ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ "ዕድገትን መምራት፤ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሐንዲሶች" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።
ከዛሬ ጥቅምት 26 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆየው የጉባኤ አካል የሆነው የአፍሪካ ሴቶችና ወጣቶች የፖለቲካ አመራር የጋራ ፎረም 2026 የመክፈቻ መርሃ ግብር በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በጋራ ፎረሙ መክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ለሥርዓተ ጾታ እኩልነት የሰጠችውን ቁርጠኝነት በሚለካ የአመራር ውጤት እየተረጋገጠ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥትም በመደመር ፍልስፍና ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሴቶችን የአመራር ሰጪነት ሚና በማላቅ ሁሉም ዜጋ በሀገር ጉዳይ እኩል የሚሳተፍበትን አቅም መፍጠሩን ተናግረዋል።
በተለይም የሴቶችን በካቢኔ ኃላፊነትና የተቋማት የአመራር ዕድል በማግኘት በፖሊሲ ፈጠራና በተለያዩ ዘርፎች እኩል ውሳኔ የሚያሳልፉበት ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።
የመደመር ፍልስፍናም ሴቶች የልማት ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆኑ እኩል ውሳኔ ሰጪ፣ አምራችና የሀገር ልማት ባለቤቶች የሚደረጉበትን ምቹ መደላድል መፍጠሩን አንስተዋል።
ይህ ውጤት ባለርዕይ አመራር፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ተቋማዊ ተግባር ይጠይቃል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ለዚህም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምስጋና አቅርበዋል።
መንግስት በመደመር እሳቤ ሴቶች በሁሉም ደረጃ መምራት እንደሚችሉ በተግባር ማሳየቱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ይህንን ተሞክሮ የፖለቲካ ፍላጎት፣ አካታች የልማት ፍልስፍናና ቀጣይነት ያለው ተግባር ሲጣመሩ ምን ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ አድርጋ እንደምታጋራ አመልክተዋል።
የሴቶች አመራርም በፖለቲካ ፓርቲዎች መዋቅር፣ በአመራር ምርጫና በእጩ አቀራረብ እንዲሁም በተቋማዊ ቁርጠኝነት ውስጥ ሊጎለብት እንደሚገባ አሳስበዋል።
አፍሪካ ዋነኛ ስትራቴጂካዊ ሀብቷ ህዝቧ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሴቶች በዚህ ረገድ አስተዋጽኦ ማድረግ እንዲችሉ ሁኔታዎች ሊመቻቹ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በፖለቲካ አመራር እኩል የተወከሉ፣ በኢኮኖሚ ህይወት የበቁና መብታቸውና ክብራቸው በተቋማት የተጠበቀ ሴቶች ያሉባትን አፍሪካ እንገንባ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ሴቶች በጾታ ወይም በሁኔታ ሳይገደቡ መሪ፣ ስራ ፈጣሪ፣ ሳይንቲስት ወይም ፖሊሲ አውጪ የመሆን ህልማቸውን የሚያሳኩበት አህጉር እንዲፈጠር መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።