የመጀመሪያው ሩብ ዓመት በተኪ ምርትና በአምራች ኢንዱስትሪ ምርቶች ወጭ ንግድ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
የመጀመሪያው ሩብ ዓመት በተኪ ምርትና በአምራች ኢንዱስትሪ ምርቶች ወጭ ንግድ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2019 (ኢዜአ)፦ በ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሶስት ወራት በተኪ ምርትና በአምራች ኢንዱስትሪ ምርቶች ወጭ ንግድ አበረታች ውጤት መመዝገቡን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሐመድ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለፁት፣ በ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በወጭ ምርት ንግድ ዘርፍ 118 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ገቢ ተገኝቷል።
ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ21 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት የታየበት መሆኑን ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በኢንዱስትሪ ተኪ ምርቶች አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ማዳን የተቻለ ሲሆን፣ ይህም የሀገራችን የንግድ ሚዛን ለማስተካከልና የውጭ ምንዛሬን ለማዳን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልፀዋል።
ከተለያዩ ሀገራት ከመጡ ባለሀብቶች ጋር በትብብር ለመስራት የተደረጉ የኢንቨስትመንት ስምምነቶች የዘርፉን ተወዳዳሪነት የሚያጎለብቱ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ስጋ አምራችና ላኪዎች ማህበር ቦርድ ፕሬዝዳንት ከሊፋ ሁሴን በበኩላቸው፣ በ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አምስት ሺህ ሜትሪክ ቶን ስጋ ወደ ውጭ በመላክ 31 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።
ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ15 በመቶ ዕድገት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
በ2019 በጀት ዓመት ወጭ ንግዱን በእጥፍ ለማሳደግ ከተያዘው ዕቅድ አኳያ በቀጣይ ወራት አፈፃፀሙን አጠናክሮ ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ድርጅታቸው በ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከወጭ ንግድ ከዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘት መቻሉን የገለጹት ደግሞ የስርጉ ኑሪ ኢብራሂም ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ ሙራድ በድሩ ናቸው።