የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የትውልዱ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ለውጤታማነቱ የድርሻችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የትውልዱ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ለውጤታማነቱ የድርሻችንን እንወጣለን
ደሴ፤ ጥቅምት 26/2019(ኢዜአ) ፦የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የትውልዱ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ለውጤታማነቱ ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ቅንጦት ሳይሆን የትውልዱ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ለውጤታማነቱ የድርሻችንን እንወጣለን።
የደሴ ከተማ ነዋሪና ወደ አሰብ በንግድ ሥራ ይመላለሱ እንደነበር የተናገሩት ወይዘሮ ከድጃ መኮንን፣ ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ከቀይ ባህር ዳርቻዎችና ወደቦች ተነጥላ አታውቅም ብለዋል።
አሰብ በቀድሞ መንግስታት በአውሳ አውራጃ ስር ይተዳደር እንደነበር የገለጹት ወይዘሮ ከድጃ፣ በደጋማ የአገራችን ክፍል የሚመረቱ የጥራጥሬ ሰብሎችንና ሌሎች ምርቶችን አሰብ ከተማ ድረስ በመውሰድ ኑሯቸውን ይገፉ እንደነበር ገልጸዋል።
የአሰብ ወደብ ለረዥም ዘመናት ባለቤትነቱ የኢትዮጵያ ለመሆኑ ምስክር እንደማያስፈልገው ጠቅሰው፣ ወደቡ ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ የሄደበት መንገድ ታሪካዊ ዳራውንና አካባቢያዊ ቅርበቱን ያላገናዘበ መሆኑን ተናግረዋል።
የባህር በር ባለቤትነትን በማጣታችን በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያስከተለውን ተጽዕኖን ለመቀልበስ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄው የትውልዱ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ በተያዘው አቋምና ቁርጠኝነት ተስፋ ማድረጋቸውን ጠቁመው፣ ለውጤታማነቱ በማንኛውም ጉዳይ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑ አረጋግጠዋል።
ሌላው የደሴ ከተማ ነዋሪ አቶ ዘሪሁን ማንደፍሮ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በሴራ የባህር በር እንድታጣ መደረጉን ጠቁመው ይህ ሁኔታም የእግር እሳት እንደሆነባቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የህዝብ ብዛት፣ እያደገ የመጣው ኢኮኖሚና ለባህር በሩ ያለን ጂኦግራፊያዊ ቅርበት፣ እንዲሁም ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ትስስራችን የትውልዱ ጥያቄ የሆነውን የባህር በር እንድናገኝ የግድ ይላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እንድትርቅ መደረጉ በሴራ የተፈጸመ የባንዳነት ተግባር ነው ያሉት ደግሞ መቶ አለቃ ጌቱ አበበ ናቸው።
ይህንን የቆየ ስብራትና የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ በመንግስትና በህዝቡ የተጀመረው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው፣ ለውጤታማነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄው ቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ትውልዱ ይህንኑ ተረድቶ ለተግባራዊነቱ በጋራ መትጋት ይጠበቅበታል ብለዋል።