ለዘላቂ አህጉራዊ ትልሞች ስኬት-የጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ሚና - ኢዜአ አማርኛ
ለዘላቂ አህጉራዊ ትልሞች ስኬት-የጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ሚና
ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ (African Political Parties Summit) ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
በጉባኤው ላይ ከመላው አፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣የፖሊሲ አውጪዎች፣የአስተዳደር ተቋማት ተወካዮች፣የሲቪል ማኅበራት፣ የወጣቶችና የሴቶች አመራሮችን እንዲሁም የልማት አጋሮችን ያሳትፋል።
ጉባኤው "ለዕድገት መምራት፡የፖለቲካ ፓርቲዎች የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ የወደፊት ዕጣ ፈንታ መቅረፅ" በሚል መሪ ሐሳብ ይካሄዳል።
መድረኩ የፖለቲካ አመራርና ፓርቲዎች በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር፣ መልካም አስተዳደርና ዘላቂ ልማት ውስጥ ያላቸውን ሚና ለመመርመር ያለመ ነው።
ጉባኤው ዛሬ በሚካሄዱ ቅድመ ጉባኤ መርሐ ግብሮች ይጀምራል።በዚህም የአፍሪካ የሴቶች አመራር ጉባኤና የአፍሪካ ወጣቶችና ፖለቲካ ፎረሞች ይካሄዳሉ።
እነዚህ መድረኮች ሴቶችና ወጣቶች በፖለቲካ ተሳትፎ፣ በአመራርና በአፍሪካ የልማት አጀንዳ ላይ ሐሳብ እንዲለዋወጡ ዕድል እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል።
በጉባኤው የፖለቲካ ፓርቲዎች ስኬታማ ኢኮኖሚን ለመገንባት ያላቸው ሚና፣የፊስካል አስተዳደር፣ የወጣቶች የሥራ ዕድል፣ ከግሉ ዘርፍ ጋር የሚኖር ትብብር፣የአየር ንብረትን መቋቋም፣አረንጓዴ ልማትና ኢንዱስትሪ በዋናነት ይዳሰሳሉ።
ኢትዮጵያም በጉባኤው ውይይቶች ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደምታደርግ ይጠበቃል።
በጉባኤው መጨረሻም የፖለቲካ ፓርቲዎች በአፍሪካ ልማት ውስጥ ሊኖራቸው በሚገባው ሚና ላይ የጋራ መርሆችን ከማስቀመጥ ባለፈ ተግባራዊ ቁርጠኝነታቸውም የሚገለጽበት ነው።
ጉባኤውን የምታስተናግደው ኢትዮጵያ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ልማት ተሞክሮዎቿን ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለማካፈል፣የመደመር ፍልስፍናዋን ለማስተዋወቅና በአህጉራዊ የፖለቲካ ውይይት ውስጥ ያላትን ተሳትፎ ለማጠናከር ዕድል ይፈጥራል።
እንዲሁም መድረኩ የአዲስ አበባን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ከማጉላት ባለፈ የኮንፈረንስ ቱሪዝምን፣ የዲፕሎማሲ ትስስርንና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።