ቀጥታ፡

በጨረቃ ብርሃን የሚካሄደው ትእይንት  

በአብዱ ይማም(ኢዜአ)


በደቡብ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የኦሞ ሸለቆ አካባቢ፣ በቱርሚ፣ በዲመካና አካባቢው የሚኖሩት የሀመሮች ባህላዊ መገለጫ እጅግ አስደናቂ ነው። በተለይም የበሬ ዝላይ ሥነ ሥርዓት፣ የኢቫንጋዲ የሌሊት ጭፈራ፣ የአለባበስና የጌጣጌጥ አደራረግና አዋዋባቸው ከልዩ መገለጫቸው መካከል ይጠቀሳሉ። የእርስ በርስ መተሳሰብ፣ የፍቅርና አብሮነታቸው እሴትም በአስደናቂነቱ ይነሳል።

የሀመሮችን ባህልና ማንነት በአለባበስ፣ በፀጉር አሠራርና ጌጣጌጦቻቸው ብሎም በኑሮ ዘይቤያቸው ለየት ይላሉ። የእርስ በርስ ግንኙነት (ማህበራዊ እሴታቸው)፣ የጋብቻና የለቅሶ ሥርዓትን ጨምሮ ሌሎችም እምቅ እሴቶች አሏቸው። የኑሮ ሁኔታቸው ከከብት እርባታ፣ ከእርሻ ስራ እና ከተፈጥሮ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ መሆኑም ይታወቃል። የከብት እርባታ ለእነርሱ የሀብት፣ የክብር፣ የማኅበራዊ ደረጃና የጋብቻ ግንኙነት መሠረት ሲሆን በግብርና ስራም በማሽላና የበቆሎ ምርት እንዲሁም በማር ምርት ይታወቃሉ።

ከወጣትነት ወደ ጎልማሳነት የሚያሸጋግረው የከብት ዝላይ ሥነ ሥርዓትም የሐመሮች ልዩ መገለጫ ነው። በሀመር ቋንቋ «ኡኩሊ ቡላ» (Ukuli Bula) በመባል የሚታወቀው ይህ ሥነ ሥርዓት ተራ የአካል ብቃት ፈተና ወይም ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ወጣት ወንዶች ከልጅነት ወደ ጎልማሳነት መሸጋገራቸውን በተግባር የሚያሳዩበት መፈተኛቸው ጭምር ነው። ሥነ ሥርዓቱ ከመካሄዱ በፊት ቤተሰብና የአካባቢው ማኅበረሰብ በተለይም አዛውንቶች ዝግጅት ያደርጋሉ። የመዝለል ስነ ስርአቱን እለት ወጣቶቹ ለዘመድ አዝማዶቻቸው በማሳወቅ ዕለቱ ሲደርስ ተሳታፊዎችና ታዳሚዎች በአንድ ስፍራ ላይ ይሰበሰባሉ።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ወንድ ወጣቶች የተደረደሩትን ከብቶች በመዝለል ብቃታቸውን ያሳያሉ። በተሳካ ሁኔታ ዝላዩን የሚያጠናቅቁት ብቁ መሆናቸው የሚረጋገጥ በመሆኑ አዲስ የዕድሜና የኃላፊነት ደረጃ የመያዛቸው ጉዳይ እውን ይሆናል ማለት ነው። ከዚህ በኋላ የጋብቻ ዕድል ከማግኘትም ባለፈ በማኅበረሰቡ ማኅበራዊ ህይወት ውስጥም የተለየ ቦታ ያገኛሉ። በመሆኑም የወጣትነት ጽናት፣ ድፍረትና ኃላፊነት ለመሸከም ዝግጁ መሆናቸው የሚረጋገጥበት የከብት ዝላይ ስነ ስርአት የሀመሮች ልዩ መገለጫ ሆኖ ቀጥሏል።

የወጣቶች የሌሊት ጭፈራ (ኢቫንጋዲ) የሚባለው ባህላዊ ስነ ስርአት ደግሞ በሀመሮች እጅግ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው ነው። ኢቫንጋዲ በተለይም በወጣቶች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ በምሽት በጨረቃ ብርሃን ታጅቦ የሚካሄድ ተወዳጅ ባህላዊ ጭፈራ ነው። በአከባበር ስነ ስርአቱ ላይ ወጣት ወንዶችና ሴቶች አምረውና ተውበው በዘፈንና በዳንስ ጨዋታውን ያደምቁታል። ወንዶች ቀጥ ብለው ወደ ሰማይ በመዝለል የአካል ብቃትና የመዝለል ግርማ ሞገሳቸውን ሲያሳዩ፤ ሴቶች ደግሞ በዘፈንና ጭፈራ ደማቅ ትእይንት ይፈጥራሉ።

የሀመሯ ወጣት የሐመሯ፤ የጠረፍ ሀገሯ ፤በጨረቃ ብርሃን አየኋት በማታ፤ ኢቫንጋዲው ቦታ። የተባለላቸው ልጃገረዶች በውበት ፈክተው፣ በደስታ ተሞልተው የሚጫወቱበት ኢቫንጋዲ የወጣቶች የትውውቅና የመተጫጫ መድረክ ብሎም የሀመሮች ባህላዊ እሴት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍበት ነው።

በሀመር ሕዝብ ዘንድ ጋብቻ የሁለት ግለሰቦች ግንኙነት ብቻ ሳይሆን የሁለት ቤተሰቦችን ትስስር የሚፈጥር ማኅበራዊ ተቋም ነው። በባህላዊው ሥርዓት የሙሽራውና የሙሽሪት ቤተሰቦች በአዛውንቶችና በአስታራቂዎች አማካይነት ይደራደራሉ። የሙሽራው ቤተሰብ ወኪል ወደ ሴቷ ቤተሰብ በመሄድ የጋብቻ ጥያቄ ያቀርባል። የጋብቻው ሂደት ከብቶችንና ፍየሎችን ጨምሮ የሀብት ልውውጥና የቤተሰቦች ስምምነትን ያካትታል። ይህ የሀብት ልውውጥ በአንድ ጊዜ የሚፈጸም ሳይሆን በስምምነቱ መሠረት በየወቅቱ ሊከናወን ይችላል።

በጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ ውስጥ ልዩ ቦታ ያለው «ዋቃቲ ቃዳ» (Waqati Qada) የተሰኘው ሥነ ሥርዓት አዛውንቶች ወይም ልዩ ሚና ያለው ሰው በሙሽራውና በሙሽሪት እጅ ላይ ቅቤ በመቀባት የጋብቻውን ትስስር ያጸናል። በሥነ ሥርዓቱ ውስጥ ሙሽሪት ለሙሽራው የተዘጋጀ የማሽላ ምግብ በማቅረብ የጋራ ሕይወታቸውን የሚያመለክት ልዩ ተምሳሌታዊ ተግባር ትፈጽማለች። ከጋብቻ በኋላም ሙሽሪት ወደ ባሏ ቤተሰቦች ስትገባ የሽግግር ሥርዓት ይኖራል። በዚህ ወቅት የፀጉር አሠራሯ፣ አለባበሷና የጌጣጌጥ አጠቃቀሟ ይለያል። የአዲሱ ቤተሰብ እናቶችና ሴቶችም በዚህ የሽግግር ወቅት የሚንከባከቧት ይሆናል።

የሀመሮች የለቅሶና የቀብር ሥነ- ሥርዓት፤ ሀዘንን የመጋራትና የመተዛዘን ጥልቅ እሴት የሚታይበት ነው። በሀመሮች ባህል መሰረት አንድ ሰው ሲሞት ዘመድ አዝማድ፣ ጎረቤቶችና የማኅበረሰቡ አባላት በቤተሰቡ ዙሪያ በመሰባሰብ የሐዘኑን ጊዜ አብረው ያሳልፋሉ። በዚህ ወቅት የሞተው ሰው ቤተሰቦችን ከማስተዛዘን ባለፈ የሥራ ጫናዎችን እንዳይሸከሙ በማገዝ ምግብ በማዘጋጀት፣ ቤትና ግቢ በማጽዳት፣ እንግዶችን በማስተናገድና ሌሎች የቀብር ዝግጅቶችን በመሸፈን የሚያግዙ ይሆናል።

የሀመር የቀብር ባህል በተለይ ለአዋቂና ማኅበራዊ ደረጃ ላላቸው ሰዎች የተለያዩ ሥርዓቶችን ያካትታል። በታሪካዊ መግለጫዎች መሠረት አንዳንድ የቀብር ሥርዓቶች ከቀብር በፊት ረጅም የሐዘንና የመታሰቢያ ጊዜን ያካትታል። የሟቹ ሕይወት፣ ጀግንነት፣ ሀብትና ማኅበራዊ አስተዋጽኦ በዘፈንና በተለያዩ የማስታወሻ ሥነ ሥርዓቶች ይገለፃል።

የሀመር ሴቶች ከቅቤና ከቀይ አፈር በተዘጋጀ ውህድ ወፍራምና ጠምዛዛ ጉንጉን በማበጀት ጸጉራቸውን ያስጌጣሉ። በተጨማሪም ከቆዳ የተሠሩ ልብሶችን፣ የብረት ሐብሎችን፣ ዶቃዎችንና ከእንስሳት ቀንድ ወይም ከባህላዊ ጥሬ ዕቃዎች የሚሠሩ ጌጣጌጦችን ያደርጋሉ። የብረት ሐብሎችና የአንገት ጌጦች የሴቷን የጋብቻ ሁኔታና በቤተሰብ ውስጥ ያላትን ደረጃ የሚያመለክቱም ናቸው። ወንዶችም የፀጉር አሠራራቸውን በልዩ መልኩ ያስውባሉ። አንዳንድ የፀጉር ቅርጾችና የራስ ላይ የሚደረጉ ጌጦች የጀግንነት፣ የአደን ወይም የማኅበራዊ ደረጃ ምልክት ሊሆኑ ይችላሉ። በመሆኑም ለሀመሮች ጌጣጌጥ የውበት መገለጫ ብቻ ሳይሆን ማንነትን፣ ዕድሜን፣ ማኅበራዊ ደረጃንና የቤተሰብ ሁኔታን የሚያሳይ ነው ማለት ይቻላል።

በሀመሮች ዘንድ አንድ ሰው ከልጅነት ወደ ወጣትነት፣ ከወጣትነት ወደ ጎልማሳነት እንዲሁም ወደ አዛውንትነት ሲሸጋገር የተለያዩ ማኅበራዊ ሚናዎችን ይረከባል። በዚህ ሥርዓት ውስጥ አዛውንቶች በጋብቻ፣ በማኅበራዊ ግጭት አፈታት፣ በባህላዊ ውሳኔና በማኅበረሰቡ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሚና አላቸው። «ቢታ» (Bitta) የሚባሉ ባህላዊ መሪዎችም በማኅበረሰቡ መንፈሳዊና ሥርዓታዊ ጉዳዮች ውስጥ የተለየ ቦታ አላቸው። በባህላዊ እምነታቸው መሠረት የበረከት፣ የዝናብ፣ የምርትና የእንስሳት ሀብት ጉዳዮች ከመንፈሳዊ ሥርዓትና ከአዛውንቶች በረከት ጋር የተያያዙም ናቸው።

ሀመሮች የሰው ጤና፣ የእንስሳት ሀብት፣ የእርሻ ምርትና የቤተሰብ ደስታ ከተፈጥሮና ከመንፈሳዊ ሚዛን ጋር የተሳሰሩ እንደሆኑ ያምናሉ። በዚህም ምክንያት በባህላዊ መሪዎች የሚከናወኑ የበረከት ሥነ ሥርዓቶች፣ ልዩ ስብሰባዎችና ማኅበራዊ ልማዶች በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ስፍራ ይይዛሉ። የሀመሮች ጥልቅ እና ድንቅ የሆነ ባህላዊ እሴትና የሀገር ሃብት በመሆኑ መንከባከብና ለዓለም ማስተዋወቅ ይገባል እንላለን።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም