የስንዴ ልማት እመርታ፡የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አይበገሬነት ማረጋገጫ - ኢዜአ አማርኛ
የስንዴ ልማት እመርታ፡የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አይበገሬነት ማረጋገጫ
ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻልና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት ውስጥ በስንዴ ልማት ዘርፍ ያስመዘገበችው ስኬት ታሪካዊና አስደናቂ እምርታ ነው።
ሀገሪቱ ለዘመናት በስንዴ ምርት ላይ የነበረባትን የውጭ ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ በማስቀረት፣በአሁኑ ወቅት ምርቱን ከውጭ ማስገባት ማቆም ችላለች።ይህ ትልቅ ስኬት ከሀገር በቀል የምርታማነት አቅም ማደግ አልፎ እስከ ምርቱን ወደ ውጭ መላክ አስችሏል።
ይህም ኢትዮጵያን በምግብ ዋስትና ራሷን የቻለች ጠንካራ ሀገር ለማድረግ የተጣለውን መሠረት በግልጽ ያሳያል።ይህ ስኬት በዘፈቀደ የመጣ አይደለም።
ኢኮኖሚያችን አይበገሬ ሆኖ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ፈተናዎችን እንዲቋቋም፣ቀድሞ መዘጋጀትና አማራጮችን ማስፋት የግድ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይገልጻሉ።
የኢኮኖሚ ፈተናዎችን በዘላቂነት ለመቋቋም አስቀድሞ መዘጋጀትና የግብርና አማራጮችን ማስፋፋት እጅግ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በባሌ ዞን ያለውን የክረምት እርሻ አፈጻጸም በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በዘንድሮው የክረምት ወቅት ከፍተኛ የዝናብ እጥረት ሥጋት በነበረበት ወቅትም ቢሆን፣በመንግሥትና በሕዝብ የተቀናጀ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መልካም አፈጻጸም መመዝገቡንና ፈተናዎችን በቅድመ ዝግጅት ማለፍ እንደሚቻል አረጋግጠዋል።
ይህ አስቀድሞ የመዘጋጀትና አማራጮችን የማስፋት የጸና ፖሊሲ ሀገሪቱ በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት ላይ እንድትበረታና ውጤታማ እንድትሆን አስችሏታል።ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን አሟልታ በማትረፏ፣ስንዴን ከውጭ ማስገባት ከማቆም አልፋ ለጎረቤት ሀገራት መላክ የጀመረችበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተፈጥሯል።
ይህ የምርት ሽግግር ግብርናን ማዘመንና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ የአማራጭ የውኃ አጠቃቀም ዘዴዎችን (እንደ መስኖ ልማት) በስፋት መተግበር ያስገኘው ቀጥተኛ ፍሬ ነው።
የኢትዮጵያ የስንዴ ልማት ጉዞ በተግባር የተረጋገጠ የኢኮኖሚ ሪፎርም ስኬት ማሳያ እና የሀገሪቱን ዘላቂ ልማት የሚያረጋግጥ ትልቅ ምሰሶ ነው።
በቅድመ ዝግጅትና በአማራጮች ላይ በማተኮር የተመዘገበው ይህ ስኬት፣ ወደፊትም የሚገጥሙ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን በራስ አቅም ለመቋቋም የሚያስችል ትልቅ መተማመኛን ፈጥሯል።
ግብርናን በዚህ መልኩ ማጠናከርና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ኢትዮጵያ ወደ ላቀ የብልጽግና ማማ ለምታደርገው ጉዞ የማይናወጥ መሠረት የሚጥል ነው።