ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ ታላቁን የመደመር ስትራቴጂ ከተልዕኮው ጋር በማጣጣም ለሁለንተናዊ ሥልጣኔ ለማበርከት ይሠራል

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 25/ 2019 (ኢዜአ)፦ምክር ቤቱ ታላቁን የመደመር ስትራቴጂ ከምክር ቤታዊ ተልዕኮው ጋር በማጣጣም ዕምቅ ሀገራዊ አቅምን በተቋማዊ ሥርዓት ለማሳደግና ለሁለንተናዊ ሥልጣኔ ለማበርከት እንደሚሰራ ተገልጿል።

 የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ  አህመድ ሽዴ በምክር ቤቱ የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ላይ ከምክር ቤቱ ጉዳዮች አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተዋል።

አፈ ጉባዔው እንደገለጹት፣ ምክር ቤቱ ታላቁን የመደመር ስትራቴጂ ከምክር ቤታዊ ተልዕኮው ጋር በማጣጣም ዕምቅ ሀገራዊ አቅምን በተቋማዊ ሥርዓት ለማሳደግና ለሁለንተናዊ ሥልጣኔ ለማበርከት ይሠራል። 

ለዚህም ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩና ዕድገትን የሚያፋጥኑ ሕጎችን በማውጣት፣ የሕዝብ ሀብት አጠቃቀምን ከሀገራዊ ቅድሚያዎች ጋር በማጣጣም እና ተቋማት ለውጤታቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ ውጤት ተኮር ክትትልና ቁጥጥር በማካሄድ ላይ ያተኩራል።

አክለውም፣ ምክር ቤቱ ዜጎችን በውይይትና በመግባባት ለመወከል፣ በፓርላማዊ ዲፕሎማሲ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ እና የኢትዮጵያን ጥቅምና ክብር በዓለም አቀፍ መድረኮች ለማስከበር እንደሚሠራ ገልጸዋል።

የሐሳብ ልዕልናን በማክበርና ስትራቴጂውን ለዜጎች ወደ ሚታይ ውጤት በመቀየር፣ ምክር ቤቱ በሥራ ዘመኑ መጨረሻ በአፍሪካ የፓርላማ ውጤታማነት ተምሳሌት የመሆን ራዕይ እንዳለው ጠቁመዋል።

ለሀገረ መንግሥት ግንባታ አቅም የሚፈጥሩ ማሻሻያዎችን መተግበር፣ ተቋማዊ ሽግግሩን በማስቀጠል ዲጂታል ምክር ቤት መገንባት እና በሰው ሀብት ልማት ለሴቶችና ለወጣቶች ትኩረት መስጠት የዕቅዱ ቁልፍ የሥራ አቅጣጫዎች መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በምክር ቤቱ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ፍቃዱ ተሰማ በበኩላቸው፣ ምክር ቤቱ ታላቁን ሀገራዊ ስትራቴጂ ወደ ሕግ፣ በጀትና ተጨባጭ ውጤት የሚቀይር የሐሳብ መድረክ ለመሆን እንደሚሠራ ገልጸዋል። 

ለሕግ አወጣጥ፣ ከስትራቴጂው ጋር ለተጣጣመ የበጀት ክትትል፣ ለውጤት ተኮር ቁጥጥር፣ ለሕዝብ ውክልናና የሐሳብ ልውውጥ፣ ለትውልድና ለሰው ሀብት ግንባታ እንዲሁም ለፓርላማዊ ዲፕሎማሲ ትኩረት እንደሚሰጥም አስረድተዋል።

የምክር ቤቱን ጽሕፈት ቤት የትንተናና የአፈጻጸም አቅም ለማጠናከር፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን፣ የምሁራንን እና ለሀገራቸው አስተዋጽኦ ማድረግ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንን አቅም ለመጠቀም እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም