ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል - የሉዓላዊነትና የዕድገት አርማ 

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ የሀገሪቱን አንድነትና ነጻነት ከማንኛውም የውስጥና የውጭ አደጋዎች በመከላከል የሰማይ ሉዓላዊነት አስተማማኝ ጋሻ ሆኖ ዘልቋል።

ተቋሙ የአየር ክልልን በንቃት ከመጠበቅ ባሻገር፣ በየጊዜው ራሱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በሰለጠነ የሰው ኃይል በማደራጀት የብሔራዊ ደህንነት ዋስትና መሆኑንም በተግባር አሳይቷል።

በዘመናዊው ዓለም ደግሞ የሉዓላዊነት እና የሰላም ዋስትና በዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ውጫዊ ኃይል የሀገርን ድንበር ወይም የአየር ክልልን ለመጣስ ሲያስብ ደጋግሞ እንዲያስብ የሚያስገድድ አቅምን መገንባት አስፈላጊ እንደመሆኑም የኢትዮጵያ አየር ኃይል ይሄንኑ ማድረግ የሚያሰችል አቅም ገንብቷል።


 

በቅርቡ መንግሥት ከሩሲያ ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት 12 ዘመናዊ 4ኛ++ ትውልድ የሆኑ የሱ-35 (Su-35) ተዋጊ ጄቶችን በይፋ መረከቡም የተቋሙን ወታደራዊ አቅም ወደ ላቀ ምዕራፍ አሸጋግሮታል።

እነዚህ ተዋጊ የጦር ጄቶች እጅግ የላቀ የአየር ላይ የበላይነት አቅም ያላቸው ሲሆን በረጅም ርቀት ራዳራቸው፣ በያዙት ቴክኖሎጂ አማካኝነት የሚሰጡት ከፍተኛ የመንቀሳቀስ ነፃነት እና በርካታ ዒላማዎችን በአንድ ጊዜ የመቆጣጠር አቅምም አላቸው።

ይህ ታሪካዊ ርክክብ ኢትዮጵያን ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ዘመናዊ የውጊያ ቴክኖሎጂ በመታጠቅ ቀዳሚዋ ሀገር እንድትሆንም አድርጓታል።


 

ይህን አስደናቂ ስኬት በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ይህ ምዕራፍ የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት ማሳያ ነው።

ይህ አቅም ጥቃቶችን አስቀድሞ ለመከላከልና ቀጣናዊ መረጋጋትን ለመጠበቅ ወሳኝ መሆኑንም ማብራራታቸው ይታወሳል።።

የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የምናደርገው ሁለንተናዊ ጥረት ዛሬ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ላይ መድርሱንም ገልጸው ኢትዮጵያ በመከላከያ ኃይል እያደረገች ያለው ዝግጁነት ጥቃትን ቀድሞ ማስቀረት የሚያስችላትን አቅም እያላበሳት ነው ብለዋል።


 

በተጨማሪም ሀገሪቱ በቀጣይ የኤስ-400 (S-400) የአየር መከላከያ ሥርዓት ባትሪዎችን እንደምትረከብ ይፋ አድርገዋል።
በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከታሪካዊ ጀግንነት ጋር በማጣመር ጦርነትን አስቀድሞ ማክሸፍ የሚያስችል ቁመና ላይ ደርሷል።

የአየር ክልላችንን አስተማማኝ ደህንነት በኤስ-400 እና በሱ-35 ጥበቃ ማረጋገጥ ደግሞ ማንኛውም አካል የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እና ሉዓላዊነት ለመድፈር ሲያስብ የወታደራዊ አቅሟን ብቃት መመልክት እራሱንም ከችግር ማዳን ግድ ይለዋል።

አየር ኃይሉ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገትና የዲፕሎማሲ ከፍታ በፅኑ መሠረት ላይ እንዲቆም የሚያደርግ፣ የኢትዮጵያን የነጻነት ታሪክ ትውልድ ተሻጋሪ በሆነ መንገድ የሚያስቀጥል እና የሰማዩን ሉዓላዊነት በታማኝነት የሚያስጠብቅ የሕዝብ አለኝታ ሆኖም ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም