በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ዘርፍ ጸጋዎችን ለይቶ በማልማት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ዘርፍ ጸጋዎችን ለይቶ በማልማት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል
ቁሊቶ፤ ጥቅምት 25/2019 (ኢዜአ):-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በግብርና ዘርፍ ያሉ ጸጋዎችን ለይቶ በማልማት የማህበረሰቡን ምርታማነት ለማሳደግና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ክልላዊ ስትሪንግ ኮሚቴ በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በሀላባ ዞን ቁሊቶ ከተማ አካሂዷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በመድረኩ እንደገለፁት፣ በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ያሉ ፀጋዎች አልምቶ በመጠቀም ማህበረሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በዚህም በክልሉ ባለፉት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ የተከናወኑ ሀገራዊና ክልላዊ ኢንሼቲቮች የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ እና የገቢና የወጪ ምርቶችን በጥራት በማምረት ተጨባጭ ውጤት ማምጣታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአቮካዶ ምርትን በስፋት አምርታ ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ የሚያስችላትና ለ15 ዓመታት የሚተገበር ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ቀርፃ ወደ ትግበራ ምዕራፍ መግባቷንም አስታውሰዋል።
በፕሮግራሙ የአቮካዶ ምርትን ለኤክስፖርት፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነትና ለሀገር ውስጥ ፍጆታ በማዋል የምግብ ዋስትናን ያረጋገጠ ማህበረሰብ ለመፍጠር ግብ መያዙንም ጠቁመዋል።
በፕሮግራሙ በክልሉ በ10 ወረዳዎች አቮካዶ የማልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ ኡስማን፣ ሥራውን ይበልጥ ለማስፋት በ44 ወረዳዎች የአቮካዶ ልማት መጀመሩን አስረድተዋል።
በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ያሉ ጸጋዎችን ለይቶ በማልማት የማህበረሰቡን ምርታማነትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱንም አስታውቀዋል።
በክልሉ የብሔራዊ አቮካዶ ልማት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ሰላሙ አብርሃም በበኩላቸው እንዳሉት የፕሮግራሙ ትግበራ ክልሉ በዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም በማሳደግ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ያሳድገዋል።
በክልሉ በባለፉት 3 ወራት 350 ኩንታል የአቮካዶ ምርት ለውጪ ገበያ ተልኮ የውጪ ምንዛሬን ለማግኘት ተችሏል ብለዋል።
በአቮካዶ ልማት እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችን በግለሰብና በተቋማት ጀረጃ በማስፋት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተያዙ ግቦችን ለማሳካት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
የስልጤ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ ሙበራ ከማል እንደገለፁት የፕሮግራሙ ትግበራ በአካባቢ ያለን ፀጋ ለይቶ በመጠቀም ረገድ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል።
በዞኑ በስልጢ ወረዳ 10 ሄክታር ማሳ በአቮካዶ እየለማ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ የፕሮግራሙ ትግበራ አርሶ አደሩን በልማቱ ያለውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማሳደጉ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ የክልል፣ የዞን ከፍተኛ አመራሮችና የፕሮግራሙ ስትሪንግ ኮሚቴዎች ተሳትፈዋል።