ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ታሪካዊ ግንኙነታቸውንና ወታደራዊ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ታሪካዊ ግንኙነታቸውንና ወታደራዊ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ ፤ አበባ፤ ጥቅምት 25/2019 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ታሪካዊ ግንኙነታቸውንና ወታደራዊ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማምተዋል።
የትልቅ ሀገር ትልቅ ሕዝብ እና ታላቅ ርዕይ
የመከላከያ ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ ከውጭ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር የሚያደርጉትን ተከታታይ የወታደራዊ ዲፕሎማሲ ውይይት በመቀጠል በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በዚሁ ወቅትም፤ ሁለቱ ሀገራት ዘመናትን የተሻገረውን ታሪካዊ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማሳደግና በወታደራዊና ስትራቴጂካዊ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር አጠናክረው ለመቀጠል ተስማምተዋል።
በውይይቱ ወቅት አቶ መሐመድ እድሪስ፤ ለፈረንሳይ አሁናዊ እና ስትራቴጂያዊ ወታደራዊ አቅምን ለማሳደግ እያደረገች ላለችው የዕውቀት ሽግግር እና የሰላም ማስከበር ተቋማዊ አቅም ለማጠናከር እያደረገች ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።
ኢትዮጵያ በቀጠናው ፍትሐዊ እና ሕጋዊ ጥቅሟን ለማስከበር ለምታደርገው ጥረት ፈረንሳይ ከጎኗ እንድትቆምም ጠይቀዋል።
በትግራይ ክልል እየተከናወነ ያለውን የትጥቅ ማስፈታትና መልሶ ማቋቋም(DDR) ሂደት በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ ፈረንሳይ ለሂደቱ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንድታደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ በበኩላቸው፤ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነትና ሁለገብ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
በተለይም በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በሚደረጉ ጥረቶች እንዲሁም በወታደራዊ ሥልጠናና አቅም ግንባታ ዘርፎች የሚከናወኑ የጋራ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።