ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ለማድረግ ምክር ቤቱ ቀዳሚ ኃላፊነት አለበት- አፈ ጉባኤ አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25 /2019 (ኢዜአ)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አህመድ ሽዴ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ለማድረግና የሀገሪቱን የተቋማዊ አቅም ለማጠናከር ምክር ቤቱ ቀዳሚ ኃላፊነት እንዳለበት ገለጹ።

ለ7ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ለምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት አመራሮች የተዘጋጀ የሥልጠና መድረክ ተካሄዷል።


 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አህመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት ባለፉት ስምንት ዓመታት የሀገሪቱን ብልፅግና ለማረጋገጥ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ማሻሻያዎች መከናወናቸውንና በዚህም በርካታ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያን ወደ ላቀ የልማት ደረጃ ለማሻገር የሚከናወኑ ተግባራት ዜጋን ማዕከል ያደረጉና በየዘርፉ ያሉ ጥረቶችን በተቀናጀ መልኩ ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚቀይሩ መሆን አለባቸው ብለዋል።

በዚህ ሂደትም የሀገሪቱን ሀብት፣ የሕዝቧን እውቀትና ተነሳሽነት፣ እንዲሁም የተቋማትን አቅም ማሰባሰብና ማቀናጀት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት በዕቅድና በአፈጻጸም ስኬት ብቻ ሳይሆን፣ በእያንዳንዱ ዜጋ ሕይወት ላይ በሚያመጣው ተጨባጭ ለውጥም መመዘን እንዳለበትም ነው አፈ ጉባኤው አስረድተዋል።

ከዚህ አንጻር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕግ አውጪነት፣ በሕዝብ ውክልናና በሥራ አስፈጻሚው ላይ በሚያደርገው ቁጥጥር አማካይነት፣ ሀገራዊ ራዕይ ወደ ተቀናጀ አፈጻጸምና ዘላቂ የዜጎች ጥቅም እንዲለወጥ የራሱን ድርሻ መወጣት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።


 

የነገዋ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነቷ የጠነከረ፣ ምርታማና መሪ ሀገር እንድትሆን ማድረግ ምክር ቤቱ ቀዳሚ ኃላፊነት እንዳለበትም አጽንዖት ሰጥተዋል።

በመሆኑም ምክር ቤቱ በሕገ መንግሥቱ የተሰጡትን ኃላፊነቶች ከምንጊዜውም በበለጠ በብቃት በመወጣት፣ የተቋማትን አቅም ለማጠናከርና የሕዝብን እምነት ለማሳደግ መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል።

ይህም የተሰጠንን ኃላፊነት መወጣት ብቻ ሳይሆን፣ ዘመኑ የሚጠይቀው አርበኝነት መሆኑን በመረዳት የኢትዮጵያን የታላቅነት ራዕይ ለማሳካት በልዩ ትኩረት መሥራት ከምክር ቤቱ የሚጠበቅ ቀጣይ የቤት ሥራ መሆኑን አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም