ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋት ብዝኅ የግብርና ምርቶችን በማምረት አዲስ የምግብና ሥርዓተ-ምግብ ደኅንነት ባህል እየገነባ ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25 /2019 (ኢዜአ)፦የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር አርሶና አርብቶ አደሩ በአነስተኛ የመሬት ይዞታ ላይ ብዝኅ የግብርና ምርቶችን በማምረት አዲስ የምግብና ሥርዓተ-ምግብ ደኅንነት ባህል እየገነባ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

የኢትዮጵያ የብዝኅ ኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ የግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና የዲጂታል ዘርፍ የምርታማነት አቅምን በማጎልበት የተሰናሰለ የዕድገት አቅም ፈጥሯል።

በግብርናው ዘርፍ ተግባራዊ የተደረጉ የልማት ተነሳሽነቶችም የእርሻ ሜካናይዜሽንና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማጎልበት የምግብ ሉዓላዊነትን እያረጋገጡ ይገኛል።

የበጋ መስኖ ስንዴ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የአረንጓዴ ዐሻራ እና የተለያዩ ወቅቶች የግብርና ልማት መርሃ ግብሮች የአርሶና አርብቶ አደሩን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት አሻሽለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በዓርባ ምንጭ ከተማ የተበሰረው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የግብርና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ እያሻሻለ ይገኛል።

መርሃ ግብሩም የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ፣ የዓሳና የንብ ማነብ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርታማነት አቅምን በማሳደግ በሀገሪቱ የምግብና ሥነ-ምግብ ደኅንነት ላይ ተጫባጭ ውጤት ማስገኘቱን ቀጥሏል።


 

ይህም የቤተሰብ ብልፅግናን በማረጋገጥና በምግብና ሥነ-ምግብ ደኅንነት ዘርፍ የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት በማሻሻል እመርታዊ የምርታማነት ምኅዳር ፈጥሯል።

በግብርና ሚኒስቴር የምግብና ሥርዓተ-ምግብ ጽሕፈት ቤት የምግብና ሥርዓተ-ምግብ አቅም ግንባታ ዴስክ ኃላፊ ያሬድ አዲሱ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ለብዝኅ የግብርና ልማት አመቺ ሀገር ናት። 

የኢትዮጵያ የተለያየ የአየር ጠባይና የሥነ-ምኅዳር ከባቢም የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የአዝዕርትና ጥራጥሬ፣ የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርታማነትን በማላቅ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል።


 

የመደመር መንግሥት የብዝኅ ኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫም ከዚህ ቀደም የነበረውን በኃይል ሰጪ የሰብል ልማት ላይ ብቻ ያተኮረ የግብርና ምርታማነት ባህል መቀየር እንዳስቻለ አስረድተዋል። 

ይህም የአርሶና አርብቶ አደሩን የግብርና ምርታማነት ብዝኅ ስብጥር በማላቅ ከራስ የምግብ ፍጆታ ባሻገር ለገበያ የሚያቀርቡበትን የተጠቃሚነት አቅም እየገነባ መሆኑን ገልጸዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የአረንጓዴ ዐሻራና የተለያዩ ወቅቶች የግብርና ልማት መርሃ ግብሮች የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የዕድገት ከባቢ መፍጠራቸውን አንስተዋል።


 

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርም የአርሶና አርብቶ አደሩን በንጥረ ነገር የበለጸገ የምግብና ሥነ-ምግብ ምርቶችን በማስገኘት ከራስ አልፎ ለገበያ ጭምር የሚያቀርቡበት አመርቂ ውጤት እያስገኘ ነው ብለዋል።

የግብርና ብዝኅ ልማት ምኅዳሩም ምርታማነትን በማላቅ በዜጎች የኑሮ ሥርዓት ላይ ቀጥተኛ ፋይዳ ያለው ለውጥ በማምጣት ጤናማ ትውልድን ማፍራት እያስቻለ መሆኑን ጠቅሰዋል። 


 

በአሁኑ ወቅትም አርሶና አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የራሱን የምግብ ፍጆታ በማሟላት የገበያ የምርት አቅርቦት ፍላጎት ላይ ጭምር በስፋት እየተሰራ ነው።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አዚዝ አያሌው በበኩላቸው፤ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የግብርና ምርታማነትን በማሻሻል አዲስ ባህል ፈጥሯል ብለዋል።


 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በዓርባ ምንጭ ከተማ የተበሰረው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በአትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳትና እንስሳት ተዋጽኦ ከፍተኛ ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል። 

ይህም አርሶና አርብቶ አደሩ በአነስተኛ ማሳ ላይ የግብርና ምርታማነቱን በማላቅ በሥርዓተ-ምግብ ላይ እመርታዊ ለውጥ እንዲያስገኝ ታስቦ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም