በአማራ ክልል የተቀናጀ የውሃና የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን በላቀ ውጤታማነት ለማስቀጠል ቅንጅታዊ አሰራር ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የተቀናጀ የውሃና የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን በላቀ ውጤታማነት ለማስቀጠል ቅንጅታዊ አሰራር ይጠናከራል
ባህር ዳር፤ ጥቅምት 25/2019 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የተቀናጀ የውሃና የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን በላቀ ውጤታማነት ለማስቀጠል ቅንጅታዊ አሰራር ይበልጥ እንደሚጠናከር የዓባይ ተፋሰስ አስተዳደር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በውሃና ተዛማጅ ዘርፎች ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የዓባይ ተፋሰስ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ መላክ በመድረኩ እንደገለጹት፤ መሬትና ውሃን በአግባቡ በማስተዳደር ትውልድ ተሻጋሪ ሀብት ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ ነው።
ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተናጠል የሚያከናውኗቸው ሥራዎች ዘላቂና ቀጣይ እንዲሆኑ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
‘‘የተቀናጀ የውሃ አስተዳደር ልማት መቋቋም ፈጻሚ አካላት ተቀናጅተው እንዲሰሩ ለማድረግ ያለመ ነው’’ ያሉት አቶ ዮሐንስ ይህም መሬትን ከመጠበቅ ባለፈ ውሃን በአግባቡ ተጠቅሞ ልማትን ለማፋጠን ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ ብቻ ከ600 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍን የተፋሰስ ልማት ሥራዎች መከናወናቸውና በቀጣይም ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ልማቱ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመላለም ምህረት በበኩላቸው እንዳሉት በክልሉ ባለፉት ዓመታት ከ8 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተሰርቷል።
የተራቆቱ አካባቢዎችን ከሰውና ከእንስሳት ንኪኪ ነጻ በማድረግና መልሶ እንዲለማ በማድረግ ውጤታማ ሥራ መሰራቱንም ጠቅሰዋል።
በዚህም ምንጮች እንዲጎለብቱ፣ የሰብል ምርታማነት እንዲጨምር እና የአፈር መከላት እንዲቀንስ ለማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ዘርፍ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታትና ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር ፕሮጀክት ተቀርፆ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩት የፕሮግራምና ሪሰርች ባለሙያ አቶ ሙሉነህ ቢምረው ናቸው።
በጣና ተፋሰስ ውስጥ ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶችና መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከውሃ፣ ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከሕብረት ስራ ማህበራትና ከግብርና ተቋማት ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው የውይይት መድረክ ላይ ከተለያዩ ተቋማት፣ ከልማት ድርጅቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የመጡ ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።