በአሰሪና ሠራተኛ መካከል ጠንካራና ጤናማ ግንኙነት መፍጠር ለተቋማት ምርታማነት ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአሰሪና ሠራተኛ መካከል ጠንካራና ጤናማ ግንኙነት መፍጠር ለተቋማት ምርታማነት ወሳኝ ነው
ጎንደር፣ ጥቅምት 25/2019 (ኢዜአ)፡- በአሰሪና ሠራተኛ መካከል ጠንካራና ጤናማ ግንኙነት መፍጠር ለተቋማት ምርታማነት ወሳኝ መሆኑን የአማራ ክልል ስራና ክህሎት ቢሮ አመለከተ።
በጎንደር ከተማ በአሰሪና ሠራተኛ ደህንነት ሕግ አፈጻጸም ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ ተካሄዷል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አማረ ዓለሙ በመድረኩ እንዳሉት፣ በአሰሪና ሠራተኛ መካከል ጠንካራና ጤናማ ግንኙነት መፍጠር ለተቋማት ምርታማነት ማደግ ወሳኝ ነው።
ለዚህም በክልሉ በሚገኙ ትልልቅ ከተሞች ከሠራተኞች መብት፣ ደህንነትና ከኢንዱስትሪ የሥራ ሥነ ምህዳር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ ሰፊ ውይይት መካሄዱን አስታውሰዋል።
የአሰሪዎችንና የሠራተኞችን መብትና ግዴታዎች የማስገንዘብ፣ በተቋማት ውስጥ የደህንነት ባለሙያዎችን የማሠልጠንና የሕግ ማዕቀፍ የማዘጋጀት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ ሥራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ ላቀው በበኩላቸው፣ የሰው ኃይል ምርታማነትን ለማሳደግ የሠራተኞችን ደህንነትና ጤንነት መጠበቅ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚሁ መሠረት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ153 በላይ በሚሆኑ ድርጅቶች ላይ የሥራ ቦታ ቁጥጥርና ክትትል የተደረገ ሲሆን፣ ጉድለት የታየባቸው ድርጅቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያስተካክሉ ግብረ መልስ ተሰጥቷል።
የጎንደር ብቅል ፋብሪካ የሰው ሀብት ልማትና አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ታምሩ እንዳሉት፣ ፋብሪካው ከሠራተኛ ማህበሩ ጋር በመቀናጀት የሠራተኞችን መብት፣ ደህንነትና ጥቅማ ጥቅም እያስከበረ ይገኛል።
በተለይም የሙያ ደህንነት መጠበቂያዎችን በማሟላትና በሥራ ቦታዎች ሊነሱ የሚችሉ የባህሪና ሌሎች ጥያቄዎችን ከሠራተኛ ማህበሩ ጋር በውይይት በመፍታት የኢንዱስትሪ ሰላም የማስፈን ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በዳሸን ቢራ ፋብሪካ አክሲዮን ማህበር የጎንደር ቅርንጫፍ የሠራተኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ዮናስ አዲሱ፣ የሠራተኞችን መብት፣ ደህንነትና ሌሎች ችግሮችን በመነጋገር የመፍታት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በፋብሪካ ደረጃ ከሚሰጡ ጥቅማ ጥቅሞች በተጨማሪ የሠራተኞችን ደህንነት፣ ጤናና የሥራ ላይ ፕሮቶኮል ሁኔታዎች ለማሻሻል በማህበራቸው ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አስረድተዋል።