የተማሪዎችን ውጤት እያሻሻለ የሚገኘው የትምህርት ቤት የምገባ መርሃ ግብር - ኢዜአ አማርኛ
የተማሪዎችን ውጤት እያሻሻለ የሚገኘው የትምህርት ቤት የምገባ መርሃ ግብር
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25 /2019 (ኢዜአ)፦የትምህርት ቤት የምገባ መርሃ ግብር በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እያገዛቸው መሆኑን የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ተማሪዎች ገለጹ።
መንግስት ከፍተኛ በጀት በመመደብ ትኩረት አድርጎ ከሚሰራባቸው ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች መካከል የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር አንዱ ነው።
በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተጀመረው የምገባ መርሃ ግብር የተማሪዎችን መጠነ ማቋረጥ በመቀነስ እና የትምህርት አቀባበላቸውን በማሳደግ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ አወንታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብሩ ያለምንም ሃሳብ ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩና ውጤታማ እንዲሆኑ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
የልዕልት ቅድመ-አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ አያንቱ ሙልጌታ፤ በትምህርት ቤት የምገባ መርሃ ግብር መኖሩ ያለምንም ሀሳብ ትምህርቷ ላይ ትኩረት እንድታደርግ እንደረዳት ገልጻለች።
ይህም በትምህርቷ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራት ከማስቻሉ ባለፈ ለወላጆቿም እፎይታ መስጠቱን ጨምራ ተናግራለች።
የምገባ መርሃ ግብሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በንቃት እንዲከታተሉ ከማድረግ ባለፈ ውጤታማ እንዲሆኑ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የተናገረችው ደግሞ የንጋት ኮከብ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዋ ሰላማዊት ፈለቀ ናት።
መርሃ ግብሩ በትምህርቷ የተሻለ ውጤት እንድታስመዘግብ ትልቅ ድጋፍ እንዳደረገላትም ተናግራለች።
የንጋት ኮከብ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ኤፍሬም ቱቾ በበኩላቸው፤ የምገባ መርሐ ግብሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡና ተሳትፎአቸው እንዲጨምር ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ተማሪዎች ሙሉ ትኩረታቸውን ለትምህርት ብቻ በመስጠታቸው ውጤታማነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።
ሌላው የዚሁ ትምህርት ቤት መምህር ተስፋዬ ወንደሙ የምገባ መርሀ ግብር መጀመር የተማሪም ሆነ የወላጅ ብሎም የማህበረሰቡን ችግር እንዲቀረፍ ትልቅ አቅም መፍጠሩን አስታውቀዋል፡፡
የልዕልት ቅድመ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ፍቃዱ ታሪክ እንዳሉት፤ የምገባ መርሐ ግብር የተማሪዎች ውጤት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሻሻል ያመጣ መርሐ ግብር መሆኑን ገልጸዋል።
በትምህርት ቤት የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው መጋቢ እናቶች መካከል ወይዘሮ አጸደ ማለዳ እና ወይዘሮ አሚናት ሁሴን በበኩላቸው፤ መርሃ ግብሩ ልጆቻቸውን ትምህርት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ከማድረግ ባለፈ የሥራ እድል እንደፈጠረላቸው ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላዬ ዘውዴ እንደገለጹት የምገባ መርሃ ግብር የተማሪዎች ሥነ-ልቦና፣ አካላዊ እድገት ብሎም የትምህርት ውጤታቸው ላይ ከፍተኛ ለውጦች እንዲመዘገቡ አስችሏል።
የምገባ መርሃ ግብሩ በሶስት መቶ ሰባ አምስት ሺህ ተማሪዎች መጀመሩን አስታውሰው፤ አሁን ላይ በትምህርት ቤት የሚመገቡ የተማሪዎች ቁጥር ከዘጠኝ መቶ ዘጠና አንድ ሺህ በላይ መድረሱን ተናግረዋል።