እንሰት- የምግብ ዋስትና መሠረት - ኢዜአ አማርኛ
እንሰት- የምግብ ዋስትና መሠረት
ጥቅምት 25 /2019 (ኢዜአ)፦ እንሰት- የምግብ ዋስትና መሠረት
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ፣ በባህላዊ እሴቶቿና በእርሻ ልማቷ የተለየች ሀገር ናት። ከእነዚህ ሀብቶቿ መካከል ለዘመናት የሕዝቦቿ የኑሮ መሠረት፣ የምግብ ዋስትና ምንጭና የባህል መገለጫ የሆነው የእንሰት ተክል ይገኝበታል።
የእንሰት ተክል ለምግብነት ከመዋሉ ባሻገር ለአፈር ጥበቃ፣ ለእንስሳት መኖ፣ ለቤት ግንባታና ለአካባቢ ሥነ-ምህዳር ጥበቃ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። በአየር ንብረት ለውጥ የኤልኒኖ ክስተት፣ የዝናብ መዛባትና ተያያዥ የተፈጥሮ አደጋ ፈታኝ በሆነበት በዚህ ወቅት እንሰት የምግብ ዋስትና መሰረት በመሆን ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ ይገኛል።
በሳይንሳዊ ስሙ Ensete ventricosum እየተባለ የሚጠራው እንሰት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቷ አካባቢዎች የግብርና ልማት ልዩ ትኩረት የሚሰጠውና የሚዘወተር ተክል ነው። የእንሰት ተክል ልዩ ባህሪው ለብዙ ዓመታት በአንድ ቦታ መቆየት፣ በተለያዩ የአፈርና የአየር ሁኔታዎች ላይ ማደግ የሚችል፣ በጥቂት መሬት ላይ ከፍተኛ የምግብ ምርት መስጠት የሚችል መሆኑም ይታወቃል።
በአየር ንብረት ለውጥ፣ በድርቅ፣ በጎርፍና በዝናብ መዛባት ምክንያት የግብርና ምርት መቀነስና የምግብ ዋስትና አስቸጋሪ በሆነበት ዓለም ውስጥ እንደ እንሰት ያሉ የምግብ አማራጮች ፍቱን መፍትሄዎች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ በገጠርና በከተሞች የሚፈለግ የምግብ አማራጭ በመሆን እያገለገለ ይገኛል።
እንሰት ውሃን በተወሰነ መጠን በግንዱና በሌሎች ክፍሎቹ ውስጥ ማከማቸት የሚችል ተክል በመሆኑ ከአንዳንድ ወቅታዊ ሰብሎች በተለየ ሁኔታ የዝናብ መዛባትን ይቋቋማል። በተለይ የዝናብ መዘግየትና የድርቅ ስጋት በሚታይባቸው አካባቢዎች ለምግብ ፍጆታነት የሚውል የምግብ ዋስትና መሰረት ነው ማለት ይቻላል።
የእንሰት ተክል በክረምት ወይንም በጋ ሳይወሰን በየትኛውም ወቅት ለምግብነት መድረስ የሚችል መሆኑም ይታወቃል። እንሰቱ ከተዘጋጀም በኋላ ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ መቆየት የሚችል ነው። በመሆኑም እንሰትን በስፋት በሚያመርቱ አካባቢዎች የብዙ ቤተሰቦች ዕለታዊ ምግብና የኑሮ ዋስትና መሰረት በመሆን እያገለገለ ይገኛል።
እንሰት በአንድ ጊዜ ተሰብስቦ የሚያልቅ ሳይሆን ተክሉ ወደ ምግብነት በሚደርስበት ወቅት እንደ ቤተሰቡ ፍላጎት በተለያየ ጊዜ መሰብሰብ ይቻላል። ይህም የቤተሰብ የምግብ አቅርቦት ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያስችል ይሆናል። የመሬት ውስንነት ያለባቸው አርሶ አደሮች በጥቂት መሬት ላይ ብቻ በማልማት የምግብ ፍጆታን ማሟላት ይችላሉ። በመሆኑም በትንሽ መሬት ላይ ብዙ ተክሎችን በማምረት ከፍተኛ የምግብ ምርት ለማግኘት ያስችላል ማለት ነው።
እንሰት በአብዛኛው ቆጮ፣ ቡላ፣ አምቾና ሌሎችም የምግብ ዐይነቶች የሚዘጋጁበት ዘርፈ ብዙ ተክል ነው። በቆጮ እና ቡላ መልክ የሚዘጋጁት ምግቦች የካርቦሃይድሬት ይዘት እንዲሁም ብረት፤ ካልሲየም፣ ዚንክ፣ ፖታሲየምና ማግኒዥየም የመሳሰሉ ማዕድናትን ይይዛሉ።
የእንሰት ተክል አስተዋጽኦ በምግብ ዋስትና ብቻ የሚወሰን አይደለም። ለአካባቢ ሥነ-ምህዳር ጥበቃ፣ ለአፈር ለምነትና ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ዘላቂነት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው። በቅጠሉ መጠንና በአቀማመጡ ምክንያት የአፈርን ገጽታን ይሸፍናል። ይህም የዝናብ ውሃ በቀጥታ አፈርን እንዳይመታና እንዳያጥበው በማድርግ የአፈር መሸርሸርን የሚከላከል ይሆናል። በተጨማሪም የእንሰት ቅጠሎችና የተለያዩ ቅሪቶቹ ወደ አፈር ተመልሰው የአፈር ለምነትን ለማሳደግ ያስችላሉ። እንሰት ከቡና፣ ከእንሰት ጥላ ተጠቃሚ ሰብሎችና ከሌሎች የደን ዛፎች ጋር በተቀላቀለ የእርሻ ሥርዓት ሊለማ የሚችል ተክል ነው።
በሌላ በኩል ከእንሰት ቅጠል ቃጫ ገመድ፣ ማሰሪያና የተለያዩ የእጅ ጥበብ ውጤቶች ይሠራሉ። ቅጠሉ ለምግብ ማሸጊያነት፣ የግንዱ ክፍሎች ደግሞ ለቤት ግንባታና ለተለያዩ የቤት ውስጥ አገልግሎቶች ይውላሉ። በዚህም እንሰት ከምግብ ፍጆታ ባሻገር ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለገቢ ማስገኛና ለገጠር ኢኮኖሚ መነቃቃት ወሳኝ ድርሻ አለው።
የእንሰት ልማት ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው በተጨማሪ ከማኅበራዊና ባህላዊ እሴቶች ጋር ጥልቅ ቁርኝት ያለው መሆኑም ይታወቃል። በእንሰት የምርትና የምግብ ዝግጅት ሂደት በተለይም ሴቶች ቆርጦ ከማዘጋጀት ጀምሮ በምግብ ዝግጅትና በምርት ማቆየት ሂደት የላቀ ሚና አላቸው።
እንሰት ያለው ሁለንተናዊ ፋይዳ ከፍተኛ ቢሆንም ልማቱንና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን መፍታት የግድ ይላል። የእንሰት በሽታ፣ የማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂ እጥረት፣ የገበያ ትስስር ደካማነትና የምርት ማቆያ ሥርዓት በጉልህ የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው።
በመሆኑም በሽታን የሚቋቋሙና ምርታማ የሆኑ ዝርያዎችን ማስፋፋት፤ የተሻሻሉ የእንሰት ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅ፤ የአርሶ አደሮችን የእርሻና የተክል ጤና አያያዝ ክህሎት ማሳደግ፤ የእንሰት ውጤቶችን ወደ ሰፊ የገበያ ሥርዓት ማስገባት፤ ለምርምር፣ ለማስፋፊያና ለግብይት የሚውሉ የተቀናጁ ድጋፎችን ማጠናከር እንደሚገባ ይመከራል።