ቀጥታ፡

በክልሉ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት ይጠናከራሉ

ቦንጋ፤ ጥቅምት 25 /2019 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ። 

ክልል አቀፍ የግብርና ልማት የንቅናቄ መድረክ "ምርታማነትን ማረጋገጥ ለክልላችን ማንሰራራትና ከፍታ"! በሚል መሪ ሀሳብ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩ የተገኙት ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ተክሌ በዛብህ እንዳሉት፣ በክልሉ ግብርና ከኢኮኖሚ የልማት ሴክተሮች መካከል ግንባር ቀደምና ሰፊ ትኩረት የተሰጠው ነው።

በክልሉ የሚከናወኑ የግብርና ልማት ሥራዎችን በንቅናቄ በመምራት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በክልሉ አርሶ አደሩ ኩታ ገጠም እርሻ፣ የግብርና ፓኬጅና የሌማት ትሩፋትን በመጠቀም ምርትና ምርታማነቱን እያሳደገ መምጣቱንም ተናግረዋል። 

በቀጣይም በገጠርና በከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማረጋገጥ እና የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ለማፋጠን የክልሉን ፀጋ ለይቶ ወደ ሀብትነት መቀየር ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም አመራሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች የአርብቶና አርሶ አደሩን ግንዛቤ ከመለወጥ ጀምሮ የተሻሻሉ አሰራሮችን መከተልና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ አቶ ተክሌ አሳስበዋል።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው እንዳሉት፣ በክልሉ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ገበያን ለማረጋጋት የተደረጉ ጥረቶች ውጤት እያስገኙ ነው።

በክልሉ አርሶ አደሩ ከተለመደው የመኸርና የበልግ አዝመራ በተጨማሪ የበጋ መስኖ ስንዴን በማልማት ተጠቃሚነቱ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

በክልሉ 93 የመስኖ አውታሮች እንዳሉ ያመለከቱት አቶ ማስረሻ፣ እነዚህና ተጨማሪ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በመስኖ በዓመት 18 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ላይ ተደርሷል ብለዋል።

በዚህም ከአራት ዓመት በፊት በክልሉ በ433 ሄክታር መሬት የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በ2018 የምርት ዘመን ወደ 5 ሺህ 778 ሄክታር ማደጉንና 190 ሺህ ኩንታል ምርት መገኘቱን ጠቁመዋል።

ዘንድሮም 10 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት የሚገኘውን ምርት ወደ 350 ሺህ ኩንታል ለማሳደግ መታቀዱን ጠቅሰዋል፡

በመደበኛ በልግ አዝመራም ልዩ ትኩረት በመስጠት የማሳ ሽፋንን አምና ከነበረበት በአሥር በመቶ በማሳደግ ከ18 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ግብ መያዙን አቶ ማስረሻ ተናግረዋል።

በሌማት ትሩፋት መርሀግብር የተመዘገበውን ምርታማነት ለማላቅ የተደራጁ መንደሮችን ሞዴል የማድረግ ሥራ እንደሚሰራ ገልጸው፤  የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ልማትም ለማስፋት በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።

እነዚህን ግብች ለማሳካት በቴክኖሎጂ የታገዙና የተሻሻሉ አሠራሮችን መከተል ይገባል ያሉት አቶ ማስረሻ፣ ምርጥ ዘርና ሌሎች ግበዓቶችን የማቅረብና የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላትን ሞዴል የማድረግ ሥራም ትኩረት እንደተሰጠው አስታውቀዋል።

በመድረኩ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም