ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ከ2019 ዓ.ም ጀምሮ የምትለካበትን አዲስ ስሌት ይፋ አደረገች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25 /2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያን አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) ከ2019 ዓ.ም ጀምሮ መለካት የሚያስችል አዲስ ስሌት በዛሬው ዕለት ይፋ ተደርጓል።

‎ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት (GDP) አንድ ሀገር በተወሰነ ጊዜ፣ በአብዛኛው በአንድ ዓመት በሀገር ውስጥ ያመረታቸውን ሁሉንም የመጨረሻ ሸቀጦች እና አገልግሎቶች በገበያ ዋጋ የሚለካ ኢኮኖሚያዊ መለኪያ ነው።

‎በዚህ መለኪያ ውስጥ የቤተሰቦች ፍጆታ፣ የንግድ ተቋማት እና የግል ባለሀብቶች ኢንቨስትመንት፣ የመንግሥት ወጪ እንዲሁም ከወጪ ንግድ የሚገኘው የተጣራ ውጤት ተደምረው ይሰላሉ።

‎ኢትዮጵያም ከፈረንጆቹ 1960 ጀምሮ የጠቅላላ ሀገራዊ ምርት መረጃዋን በይፋ ስታሳውቅ ቆይታለች።

ሆኖም እስካሁን ሥራ ላይ የነበረው የ2008 ዓ.ም የመነሻ ዓመት ስሌት በኢኮኖሚው የተፈጠሩ አዳዲስ ለውጦችን እና የዘርፎችን መስፋፋት በበቂ ሁኔታ የሚያንፀባርቁ አለመሆናቸው ተገልጿል።

‎የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር አቶ በረከት ፍስሃጽዮን የቀድሞው የኢኮኖሚ መለኪያ የዲጂታል የገንዘብ ልውውጦችን፣ እንደ ካፒታል ገበያ፣ የበጋ መስኖ ልማትና የኮሪደር ልማት ያሉ አዳዲስ የኢኮኖሚ ልማቶች መረጃዎች ያልተካተቱበት፣ አዲስ የኢኮኖሚ ቅርፅ በአሮጌ መለኪያ ሲለካ የቆየበት መሆኑን ተናግረዋል።

‎አዲሱ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ኢኮኖሚ ስሌት በቅርቡ የተካሄዱ የግብርና ቆጠራን፣ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራን እና የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት መረጃዎች የተካተተበት ወቅታዊ የሆነ የኢኮኖሚ ሁኔታን የሚያመለክት መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲሱ ስሌት የኢትዮጵያ የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት 210 ቢሊዮን ዶላር መድረሱም በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

‎አዲሱ ስሌት የሀገራችንን አሁናዊ የኢኮኖሚ ሁኔታን የሚያመላክት፣ ለፖሊሲና ዕቅድ ትክክለኛ ግብዓት በመሆን እንዲሁም ከአጋር አካላት ጋር የምታደርገውን ድርድር አቅም ከፍ የማድረግ ጠቀሜታ እንዳለው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም