የሀገር ውስጥ ምርትን አለካክ ወቅታዊ የማድረግ ስራ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በተገቢው መንገድ የለካና ተዓማኒነት ያለው ስሌት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር ውስጥ ምርትን አለካክ ወቅታዊ የማድረግ ስራ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በተገቢው መንገድ የለካና ተዓማኒነት ያለው ስሌት ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25 /2019 (ኢዜአ)፦የሀገር ውስጥ ምርትን አለካክ ወቅታዊ የማድረግ ስራ ዘመኑን የዋጀ፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ትክክለኛ መጠንና እድገት በአግባቡ የለካ እንዲሁም ተዓማኒነት ያለው ስሌት መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።
የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት የተሻሻለውን ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ግመታን ወቅታዊ የማድረግ ስራ ይፋ አድርጓል።
በዚህም የተሻሻለው የጠቅላላ ሀገር ውስጥ ምርት መረጃ ቋሚ ዓመት ከ2008 ወደ 2017 ዓ.ም እንዲቀየር ተደርጓል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር በረከት ፍስሀጽዮን ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት የሁሉም ነገር መለኪያ ነው።
የጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ስሌት የተሳሳተ ወይም ጊዜውን ያልዋጀ ከሆነ ትክክለኛ ዕቅድና መረጃ ለማግኘት ያስቸግራል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተደረገው የቋሚ ዓመት ለውጥ መሠረታዊ መረጃን መሠረት ያደረገና ብዙ አዳጊ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገራዊ የፋይናንስ ጥልቀትን ለመለካት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ቁጠባን ወደ ምርታማ ዘርፍ ለማሸጋገር ያስችላል ብለዋል።
የኢንዱስትሪ፣ የግብርና፣ የቴክኖሎጂ እና ሌሎችም የኢኮኖሚ ዘርፎችን ትክክለኛ ዋጋና ቦታ አመላካች መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አቅጣጫ የሚያቀላጥፍ፣ ትንበያና የዕድገት ግምትን ወቅታዊ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
ለውጡ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በተሻለ ሁኔታ ማወቅ ያስችላል ብለዋል።
የኢትዮጵያን የተሟላ ኢኮኖሚ በአግባቡ የለካ፣ በማደግ ላይ ያሉ አዳዲስ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ያካተተ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተዓማኒነትን ለዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት የሚያስተዋውቅ፣ ተዓማኒና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሥራ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው ብለዋል፡፡