ቀጥታ፡

በሶማሌ ክልል የቱሪስት መዳረሻዎችን በመገንባትና በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል 

ጅግጅጋ፤ ጥቅምት 25 /2019 (ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን በመገንባት፣ በማስተዋወቅና መሠረተ ልማትን በማሟላት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ መሀሙድ በይነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል።


 

ለዚህም የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎችን በመገንባት፣ በማስተዋወቅና መሰረተ ልማትን በማሟላት የዘርፉን ገቢና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ክልሉን የቱሪዝም ስበት ማዕከል ለማድረግ የተሠሩ ሥራዎችን ያነሱት አቶ መሀመድ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ የተሰራውና የገበታ ለትውልድ አካል የሆነው የሸበሌ ሪዞርትን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ሪዞርቱ ከጂግጂጋ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ለመዝናኛነት በብዙዎች ተመራጭ መሆኑን ገልጸው፣ ቀጣናዊ የቱሪዝም ልማትን በማሳደግ በክልሉ የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።


 

የክልሉ የቱሪዝም ልማት ሥራዎች ከዘርፉ የሚገኘውን ጠቀሜታ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ጠቅሰው፣  በጂግጂጋ ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ሥራም ለቱሪስት ፍሰት መጨመር አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።

በክልሉ ያሉ የቱሪዝም ሀብቶችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የማስተዋወቅ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘርፉ ለሥራ ዕድል ያለውን ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን ይበልጥ ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል።


 

እንደ አቶ መሀሙድ ገለጻ፣ በክልሉ የኤረር ጎታ እና የአራቢ ፍልውሃ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎችን መሠረተ ልማት የማሟላትና የማስተዋወቅ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።

በክልሉ ታሪካዊ ቅርሶች ከመጠበቅና ከመንከባከብ ባለፈ በአግባቡ እንዲተዋወቁ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም