የራስን አቅም የማሳደግ ዕቅድ መተግበሩ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ዕድገትና ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል - ኢዜአ አማርኛ
የራስን አቅም የማሳደግ ዕቅድ መተግበሩ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ዕድገትና ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል
ነቀምቴ፤ ጥቅምት 25 /2019 (ኢዜአ)፦ የራስን አቅም የመጠቀምና የማሳደግ ዕቅድን በቁርጠኝነት መተግበር የሕዝቡን ሁለንተናዊ ዕድገትና ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያግዝ የምዕራብ ኦሮሚያ ዞን አስተዳዳሪ አቶ መስፍን መላኩ ገለጹ።
በምዕራብ ኦሮሚያ ዞን የሚገኙ የዞን፣ የከተማ እና የወረዳ የመንግሥትና የፓርቲ አመራሮች የራስን አቅም የመጠቀም ስትራቴጂካዊ ዕቅድን በውጤታማነት ለመተግበር የሚያስችላቸው ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የምዕራብ ኦሮሚያ ዞን አስተዳዳሪ አቶ መስፍን መላኩ በዚሁ ወቅት፤ ባለፉት ዓመታት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ዘርፎች የተመዘገቡ በርካታ ድሎች ሕዝቡን ወደ ከፍተኛ የልማት ደረጃ የሚያሸጋግሩ ጠንካራ መሠረቶችን የጣሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም ኢኮኖሚውን በብቃት መምራት የሚችል አቅም ያለው አመራር በማፍራት፤ የተለያየ መሠረት ያለውና የተለያዩ ጫናዎችን መቋቋም የሚችል ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተደረገው ጥረት ተጨባጭ ውጤት እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተያዙት የልማት ግቦች አንጻር አሁንም መድረስ ከሚገባው ደረጃ ላይ ሙሉ በሙሉ እንዳልተደረሰ አመልክተዋል።
ችግሮችን ከሥር መሠረታቸው ለመፍታት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የራስን አቅም ለማሳደግ በወጣው ዕቅድ በመመራት ሁለንተናዊ ሽግግርን ለማረጋገጥ እንደሚሠራም አመልክተዋል።
የራስን አቅም የማሳደግ ዕቅድ ምርታማነትን ከማረጋገጥ ባለፈ በሁሉም ዘርፎች ዘላቂ ዕድገት ለማምጣት የሚያስችል መሆኑንም አቶ መስፍን ገልጸዋል።
በዞኑ እየተሰጠ ያለው ሥልጠና የዕቅዱን ዓላማ፣ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎችና መሠረታዊ መርሆዎች በተመለከተ የአመራሮችን ግንዛቤ ለማጠናከርና ዕቅዱን በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች ወደ ተግባር ለመቀየር ዝግጁነት ለመፍጠር ያለመ ነውም ብለዋል።
ዕቅዱን ለማሳካት ያሉ የልማት ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም፣ የሰው ኃይልን በእውቀትና በሙያ ማብቃት፣ ምርታማነትን ማሳደግ፣ ኢንዱስትሪያላይዜሽንን ማስፋፋትና ተጠያቂነት ያለው የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ትኩረት እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል።
ከሥልጠናው በኋላ ተሳታፊዎች ያገኙትን ግንዛቤ በዕለት ተዕለት ሥራቸው በመተግበር ዕቅዱ በማኅበረሰብና በቤተሰብ ደረጃ ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጣ የድርሻቸውን እንዲወጡ ይጠበቃልም ብለዋል።