በካፋ ዞን የደረሱ ሰብሎችን ከብክነት በፀዳ መልኩ የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በካፋ ዞን የደረሱ ሰብሎችን ከብክነት በፀዳ መልኩ የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ ነው
ቦንጋ ፤ ጥቅምት 25 /2019 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በካፋ ዞን የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሹ ከብክነት በፀዳ መልኩ የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ሕብረት ስራ መምሪያ አስታወቀ።
በዞኑ የሺሾእንዴ ወረዳ አርሶ አደሮች የደረሰ የጤፍ ሰብላቸውን በተደራጀ መልኩ በጥንቃቄ እየሰበሰቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የዞኑ ግብርናና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ አቶ አትርሴ ሸታቸው፣ ዞኑ ለግብርና ሥራ ምቹና ሰፊ የመልማት አቅም ያለው መሆኑን ገልጸው፣ ይህንን አቅም በተገቢው በማልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ባለፉት ጊዜያት ዘርፉን የማዘመን፣ የግብዓት አጠቃቀምን የማሳደግና የማይታረስ መሬትን ዜሮ የማድረግ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
በ2018/19 የመኸር ወቅት ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ ባቄላ፣ አተርን በመሳሰሉ ዋና ዋና ሰብሎች ከ131 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈን መቻሉን ኃላፊው ገልጸዋል።
ምርታማነትን በሄክታር ወደ 25 ኩንታል በማሳደግ በአጠቃላይ ከለማው ማሳ 3 ሚሊዮን 361 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት ግብ መጣሉን ተናግረዋል።
ከጥቅምት አጋማሽ ጀምሮ ቀድመው የሚደርሱ ጤፍና አተርን የመሳሰሉ ሰብሎችን የመሰብሰብ ሥራ ከብክነት በፀዳ መልኩ በጥንቃቄ እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።
በዚህም እስካሁን ከ3 ሺህ 232 ሄክታር በላይ ማሳ ላይ ያለ አተርና ጤፍ መሰብሰቡንና ከዚህም 52 ሺህ 972 ኩንታል ምርት ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።
በዞኑ የሺሾእንዴ ወረዳ አርሶ አደሮች በበኩላቸው፣ የደረሰ ጤፍና ሌሎች ሰብሎችን በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ከብክነት በፀዳ ሁኔታ በጥንቃቄ እየሰበሰቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በወረዳው የዋረታ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አዱኛ ገብረየሱስ፣ ለ14 ሆነው በማህበር በተመቻቸላቸው ሰባት ሄክታር መሬት ላይ በባለሙያ ምክረ ሀሳብ ታግዘው በመኸር ወቅት በሙሉ ፓኬጅ ጤፍና ቦሎቄ ማልማታቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በቆሎ አምርተው ጥሩ ጥቅም ማግኘታቸውን ጠቁመው፣ ምርቱ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ በተደራጀ መልኩ በጥንቃቄ እየሰበሰቡ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
ሌላኛው የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር ዝናቡ አማረ፣ ለሰባት ሆነው በስድስት ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን የጤፍ ምርት በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ምርቱን ከብክነት በፀዳ መልኩ እየሰበሰቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ ተከታታይነት ያለው የባለሙያ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
የደረሰውን ምርት ካነሱ በኋላ በቆሎ ለመዝራት የማሳ ዝግጅት መጀመራቸውንም አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል፡፡