በምስራቅ ጎጃም ዞን የአካባቢን ጸጋ በመጠቀም የሥራ እድል የመፍጠር እንቅስቃሴ ውጤት እያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ጎጃም ዞን የአካባቢን ጸጋ በመጠቀም የሥራ እድል የመፍጠር እንቅስቃሴ ውጤት እያመጣ ነው
ደብረ ማርቆስ፤ ጥቅምት 25 /2019 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ ጎጃም ዞን የአካባቢን ጸጋ በመጠቀም የሥራ እድል የመፍጠር ሥራ ውጤት እያመጣ መሆኑን የዞኑ ሥራ እና ክህሎት መምሪያ ገለፀ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ፀሐይ ቦጋለ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በምስራቅ ጎጃም ዞን የአካባቢን ጸጋ በመጠቀም የሥራ እድል የመፍጠር ሥራ ውጤት እያመጣ ነው።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ከ141 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተተገበረ ሲሆን፣ ባለፉት ሦስት ወራት ለ14 ሺህ 476 ወገኖች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል።
በተፈጠረው የሥራ እድል ተጠቃሚ ለሆኑ ዜጎችም ከ23 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር እና ከ180 በላይ የመስሪያና መሸጫ ኮንቴይነሮችን ማመቻቸት መቻሉን ተናግረዋል።
ሥራ የተፈጠረላቸው ወጣቶች በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን፣ በኮንስትራክሽን፣ በግብርና፣ በአገልግሎት እና በመሳሰሉት ዘርፎች መሰማራታቸውን ገልጸዋል።
በቀሪ ወራትም እቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በባሶሊበን ወረዳ የጁቤ ከተማ ነዋሪ ወጣት ትዕግስት በለጠ እንደገለጸችው፣ አራት ሆነው በመደራጀት በእንቁላል ጣይ ዶሮ እርባታ ሥራ ተሰማርተው እየሰሩ ነው።
በአሁኑ ወቅትም በተመቻቸላቸው የብድርና የመስሪያ ቦታ ከሁለት ወር በኋላ እንቁላል መጣል የሚጀምሩ ከአንድ ሺህ በላይ ዶሮዎችን የመንከባከብ ሥራ እየሰሩ እንደሆነ ተናግራለች።
በዚህ ዓመት አምስት ሆነው በመደራጀት በኮንስትራክሽን ዘርፍ ተሰማርተው እየሰሩ መሆናቸውን የገለጸው ደግሞ በአዋበል ወረዳ የሉማሜ ከተማ ነዋሪው ወጣት ዘላለም ልየው ነው።
ሥራውን ከጀመሩ አጭር ጊዜ ቢሆንም ውጤታማ ሆነው ለመዝለቅ በትጋት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጿል።
በዞኑ ባለፈው በጀት ዓመት ከ115 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም ተመላክቷል።